AMN-የካቲት 15/2017 ዓ.ም
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን የላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ በሰሜን ሸዋ አካባቢ ለሚንቀሳቀሰው የሸኔ ሽብር ቡድን ሊተላለፉ የነበሩ በርካታ የመገናኛ ሬዲዮኖች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የመገናኛ ሬዲዮኖቹ የደቡብ ቀጣና በሚል ከሚጠራው የሸኔ የሽብር ቡድን ክንፍ የተላኩ መሆኑን በመረጃ ስምሪት ተረጋግጦ ክትትል ሲደረግ እንደነበር ያመለከተው አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ፤ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ሱሉልታ ልዩ ስሙ ሚዛን የሚባል አካባቢ በጸጥታ ኃይሎች አማካኝነት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ጠቁሟል፡፡
በሕገ-ወጥ ድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን ትስስር በመለየትም እርምጃ መወሰዱን ገልጿል፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያቶችም የሽብር ቡድኑን በሎጀስቲክስ፣ በመሣሪያና በፋይናንስ ለማጠናከር ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች የተቀናጀ የመረጃ ስምሪት በማከናወን ከፌዴራልና ከክልል የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ሲከሽፉ እንደነበር መረጃው አስታውቋል፡፡
ለሽብር ተግባር ሊውሉ የነበሩ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት ዩኒፎርሞቸና ሌሎችም ቁሶች ተጠቃሽ መሆናቸውን አስታውሷል፡፡
በሰሜን ኬንያ የሚንቀሳቀሰው የሸኔ ሽብር ቡድን የሀገሪቱ የጸጥታ አካላት ባከናወኑት የተቀናጀ ኦፕሬሽን ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ደርሶበት እየተበተነ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን የላከው መረጃ አስታውሷል፡፡