በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል ማህበረሰቡ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ

You are currently viewing በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል ማህበረሰቡ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ

AMN ህዳር 16/2017 ዓ .ም

በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል ማህበረሰቡ በተቀናጀ መንገድ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

“የሴቷ ጥቃት የኔም ነው፤ ዝም አልልም” በሚል መሪ ሃሳብ ዓለም አቀፍ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን በድሬዳዋ አስተዳደር እየተከበረ ነው።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሐረጓ ማሞ እንደገለፁት፤ የሴቶችን ፆታዊ ጥቃት የመከላከል ተግባር የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው።

”ችግሩን ለመከላከል እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ለውጥ እያመጡ ቢሆንም ከስፋቱ አንፃር አሁንም የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይገባል” ብለዋል።

በዓለም ለ33ተኛ ጊዜ በሀገራችን ለ19ተኛ ጊዜ በድሬደዋ እየተከበረ የሚገኘው የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ጥረት ለማሳደግ እና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማጎልበት እንደሚያስችል መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በበዓሉ ላይም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ እና የብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ዛሐራ ሁመድ፣ የድሬደዋ አስተዳደር ምክርቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደን፣ የፌደራል እና የክልሎች የዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ዛሬ በድሬደዋ መከበር የጀመረው አለም አቀፉ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም በተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚከበርም ለማወቅ ተችሏል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review