- ከ87 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት የሚሸፍኑ የመንገድ ግንባታ ስራዎች ተከናውነዋል
- በግማሽ ዓመት ለተከናወኑ ሥራዎች 10 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ ውሏል
- ለ5 ሺህ 611 የስራ ፈላጊዎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የጀነራል ካውንስል አባላትና በየደረጃው የሚገኙ የሥራ መሪዎች በተገኙበት ጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ያዘጋጀ ሲሆን በአፈፃፀሙና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በዕለቱ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በ2017 በጀት ዓመት የተቋሙን መደበኛ ስራዎች እና የሁለተኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራዎች በላቀ ሁኔታ ለመፈፀም እንዲሁም ተቋማዊ የሪፎርም ስራዎችን ለማከናወን በቂ ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ወደ ተግባር ተገብቶል። በዚህም ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በስድስት ወራት 483 ነጥብ 23 ኪሎ ሜትር የግንባታና የጥገና ስራዎች ለማከናወን አቅዶ ከዕቅዱ በላይ 748 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍኑ ልዩ ልዩ የመንገድ ግንባታና የጥገና ስራዎች ማከናወን ችሏል፡፡ ይህም ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ34 ነጥብ 7 በመቶ የአፈፃፀም ብልጫ ያሳያል፡፡
ባለፉት 6 ወራት ከ87 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት የሚሸፍኑ ልዩ ልዩ የመንገድ ግንባታ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከልም በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የተገነቡትን መንገዶች ጨምሮ 25 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የአስፋልት፣ 8 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የጠጠር፣ የድሬኔጅና ድጋፍ ግንብ ግንባታ 0 ነጥብ 9፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የኮብል መንገድ ግንባታ 0.59 እና 33 ነጥብ 95 ኪሎ ሜትር የኮብል ንጣፍ መንገድ ስራዎች እንዲሁም 18 ነጥብ 24 ኪሎ ሜትር ነባር የእግረኛ መንገዶችን ለማዘመን የመልሶ ግንባታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ከግንባታ ስራዎች ጎን ለጎን በተለያዩ ምክንያቶች ለብልሽት የተዳረጉ 52 ነጥብ 08 ኪሎ ሜትር የአስፋልት፣ 7 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የጠጠር፣ 0 ነጥብ 64 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ መከለያ አጥር አዲስ ግንባታ እና የጥገና ስራ፣ 388 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የድሬኔጅ መስመሮች ፅዳት፣ 3 ነጥብ 21 ኪሎ ሜትር የድሬኔጅ መስመር ዕድሳትና ጥገና፣ 16 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ ጥገናና የከርቭስቶን ስራዎችን አከናውኗል፡፡
ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በስድስት ወራት ውስጥ ካከናወናቸው ሥራዎች መካከል ከዕቅድ ውጭ ያከናወናቸው የመንገድ ማስፋፊያ ሥራዎች የስኬታማነቱ ማሳያ ናቸው፡፡ ከዕቅድ ውጪ ከተሰሩ ስራዎች መካከልም በመንገድ ጥገና ዘርፍ በዘመቻ መልክ የብላክ ስፖት (የተቦረቦሩ/ የተበላሹ አስፓልት መንገድ) የመጠገን ስራዎች እንዲሁም በከተማው ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በመሰራቱ የከተማዋን የጎርፍ አደጋ ለመቀነስ ተችሏል፡፡
ከዮርዳኖስ ሆቴል እስከ ሴቶች አደባባይ፣ ፓላስ አቧሬ መንገድ ፕሮጀክት፣ ሃይሌ አለም ካዛንቺስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ከዕቅድ ውጭ ግንባታቸው በመከናወን ላይ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በመዲናዋ በርካታ የግንባታና የጥገና ስራዎች በመደበኛ እና በኮሪደር ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን ከአስተዳደሩ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት በድምሩ በ44 ሺህ 389 ሜትር እስኩዌር ስፋት ያለው 17 የተሽከርካሪ ማቆሚያ (Parking Areas) ተገንብተዋል፡፡ ይህም በከተማዋ ሰፊ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር አድርጓል፡፡
የተቋሙ የመደበኛ እና ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ስራዎች የግብዓት እጥረት እንዳይገጥማቸው 1 ነጥበ 01 ቢሊዮን ብር የሚገመት ግብዓት ማምረት ከመቻሉም በላይ የአስፋልት ፕላንት ተከላ ተጠናቅቆ ምርት ማምረት ጀምሯል፡፡
በኮሪደር ልማት ሳቢያ ከካዛንቺስ ተነስተው ገላን ጉራ የመኖሪያ መንደር ለገቡ ነዋሪዎች የዝቅተኛ ወጪ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይት ላይ የዋና መዳረሻ መንገድ ግንባታና የአውቶብስ ማቆሚያ ግንባታ በአስፋልት ንጣፍ ደረጃ ተከናውኗል፡፡ በተጨማሪም አያት 2 (ጨፌ)፣ ቦሌ አራብሳ 5 እና 6 ኮንዶሚኒየም ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን (ኢኮስኮ) ጋር ያለውን ውል በማቋረጥ በማህበረሰቡ ይቀርቡ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመመለስ ከኮሪደር ልማት ጋር ለሚነሱ የልማት ተነሺዎች የመንገድ መሰረተ ልማት የማሟላት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በግማሽ ዓመት ውስጥ ላከናወናቸው ሥራዎች 10 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ አውሏል፡፡ ለተመዘገበው ውጤታማ አፈፃፀም ለኮሪደር ማሻሻያ የልማት ስራ ሰፊ ትኩረት የተሰጠው መሆኑ፣ በከተማው ለእግረኛ መንገድ መልሶ ማልማት ስራዎች ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ መደረጉ እንዲሁም በተለያዩ የመንገድ ጥገና ስራዎች ግብዓትና የኮንስትራክሽን መሳሪያዎችን በቅንጅትና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ቀን ከሌሊት በርብርብ መሰራቱ ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸው የአፈፃፀም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
ባለስልጣኑ ለቀጣይ የስራ እንቅስቃሴ ተግዳሮት ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ ከለያቸው መካከል የወሰን ማስከበር ሥራ አንዱና ዋነኛው ችግር መሆኑ ተጠቅሷል። ይህን ችግር ለመቅረፍ የወሰን ማስከበር ችግር ያለባቸው ፕሮጀክቶች ከጨረታ በፊት መፍትሔ እንዲያገኙ እንዲሁም በምንዛሬም ለውጥ ምክንያት በፕሮጀክቶች ላይ የሚመጣውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል፡፡ ተቋሙ በመንገድ ወሰን ውስጥ የሚገኙ 384 ቤቶች፣ 266 የመብራት እና 98 የቴሌ ፖሎችን ያስነሳ ሲሆን ለዚህም በጠቅላላ 1 ነጥብ 68 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጓል፡፡
ሌላው እንደ ተግዳሮት የተጠቀሰው የግንባታ ግብዓቶች እጥረት ሲሆን፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ ተመርቶ የተከማቸ የኮብልስቶን ምርት ጥቅም ላይ እንዲውል፣ ለሰብ-ቤዝ ዝግጅትና ለኮብልስቶን ስራዎች ትኩረት በመስጠት ሥራዎች እንዲሰሩ ማድረግ፣ የሲሚንቶና የኮንክሪት አቅርቦት ችግር መፍትሔ እንዲያገኝ ማድረግ እንዲሁም አብዛኞቹ ክሬሸሮች ያረጁና ብዙ ዓመት ያገለገሉ በመሆናቸው ዘላቂ ጥገና እንዲደረግላቸው ማድረግ በተቋሙ እንደ መፍትሄ ተቀምጧል፡፡
በተጨማሪም ደካማ አፈፃፀም ያላቸው ስራ ተቋራጭ እና አማካሪዎች ላይ በውሉ መሰረት ጥብቅ ክትትል፤ ወጥ የሆነ የስራ ተቋራጮች መመዘኛ መስፈርት እንዲኖር ማድረግ እና ተጫራቾች የሚያውቁበትን መንገድ ማመቻቸት የሚሉትንና ሌሎችም ችግሮች ሊቀርፉ የሚችሉ አሰራሮች ላይ ትኩረት በማድረግ የበጀት ዓመቱን ግብ ለማሳካት ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራ መሆኑ በሪፖርቱ ማጠቃለያ ላይ ቀርቧል።
ተቋሙ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ለ5 ሺህ 611 የስራ ፈላጊዎች የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ከመደበኛ ሥራዎች በተጓዳኝ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ችግረኛ እና ወላጅ አልባ ህፃናትን እንዲሁም ከኤች አይ ቪ ጋር ለሚኖሩ የተቋሙ ሰራተኞች የሚያደርገውን ድጋፍ መቀጠሉም በሪፖርቱ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡
የቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ በተሳተፊዎች ከቀረቡ ሃሳቦች መካከል የተቋሙ የስድስት ወራት አፈፃፀም አበረታች ቢሆንም አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የወሰን ማስከበርና ሌሎች ችግሮች በወቅቱ ተለይተው የማስተካከያ እርምጃዎች ሊወሰድባቸው ይገባል የሚል ይገኝበታል፡፡
የጠጠር እና የኮብል ስቶን መንገዶች ግንባታ በተመለከተም በቀጣዮቹ ወራት ትኩረት ሰጥተን መስራት ይጠበቅብናል የሚል ሃሳብም ቀርቧል፡፡ በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት የተገኙ ስኬቶችና መልካም ተሞክሮዎችን በማሳደግ፣ በቀጣይ ወራትም የተቋሙን ውጤታማነት ለማስቀጠል ሁሉም የተቋሙ አመራርና ሠራተኛ በላቀ ቅንጅትና ትጋት መስራት እንደሚጠበቅባቸው የተናገሩት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጅኒየር ታከለ ሉለና ናቸው፡፡
በስራ ተቋራጮች ሲገነቡ የነበሩና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ግንባታቸው የተጓተተ የመንገድ ፕሮጀክቶች ችግሮችን በመፍታት የግንባታ ሥራዎችን ማስቀጠል መቻሉን የጠቆሙት ደግሞ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሬጉላቶሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ፀጋዬ ቦርሴ ናቸው፡፡ በአስተያየታቸውም የመፍትሔ አማራጮችን በአግባቡ ባለመጠቀም የመፈፀም ጉድለት ካሳዩ የስራ ተቋራጮች ላይ ፕሮጀክቶችን በመረከብ፣ በራስ ኃይል እንዲገነቡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት ለትራፊክ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ የነበሩ መንገዶችን በዘመቻ መልክ በስፋት በመጠገን በከተማዋ ምቹ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር መሰራቱን ያስታወሱት የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የመንገድ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር መሐመድአወል ሰይድ ሲሆኑ እሳቸውም በአገልግሎት ላይ የሚገኘውን የመንገድ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም፣ በመንከባከብና በጋራ በመጠበቅ ረገድ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የጋራ ኃላፊነቱን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የውይይቱን የማጠቃለያ መልዕክት ያስተላለፉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሙህዲን ረሻድ በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት የግንባታና ጥገና ስራዎች የተሻለ አፈፃፀም እንደነበራቸው ገልፀው ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ተልዕኮውን በብቃት መወጣት ይችል ዘንድ፤ በአደረጃጀት፣ በቴክኖሎጂ እና በአሠራር የተሻለ ተቋም ለመፍጠር የሪፎርም ስራዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ ተቋሙ በየዘመኑ እየተገነባ የመጣ ነው፡፡ ይሁንና ወቅቱን የሚመጥን ተቋም ከማድረግ አንፃር መሟላት ያለባቸው ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የተጓተቱ አንዳንድ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ በከተማ አስተዳደሩ በማስወሰን ወደ ተግባር እንዲገባ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከግብዓት ማምረቻ እና አፈር መድፊያ ቦታዎች እጥረት ጋር በተያያዘ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ በዕቅድ አካትቶ መሥራት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡
በመጨረሻም ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ የተሸጋገሩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ሙሉ በሙሉ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግና በክረምት ወራት የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ ስጋት ለመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ከሌሎች የመንገድ ዘርፍ ሥራዎች ጋር ተቀናጅተው ከወዲሁ በልዩ ትኩረት እንዲሰሩ በማሳሰብ ሀሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
በሳሙኤል ዮሐንስ