AMN-መጋቢት 1/2017 ዓ.ም
ከ699 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥረው ሶስተኛው የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በተገኙበት በጅማ ከተማ ይፋ ሆኗል።
ሚኒስትሯ በማስጀመሪያ መርሃ ግብር እንዳሉት ፕሮጀክቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን ህይወታቸውን ያሻሽላል።
ለቀጣይ ሶስት ዓመታተ የሚተገበረው ፕሮጀክቱ በሀገሪቷ በተለያዩ ከተሞች ከ699 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የሚያመቻችና ብዙዎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት የሚቀይር መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ዜጎች ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ ተተግብሮ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ከኮሪደር ልማት ጋር ተጣጥሞ እንደሚተገብር ገልፀው፣ ከተሞቻችን ውብ፣ ጽዱና አረንጓዴ ሆነው ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እንዲሆኑ በትብብርና በቅንጅት የሚሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጣሃ ቀመር በበኩላቸው ልማታዊ ሴፍትኔቱ ለከተማችን ውበት አጋዥ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖቻችን የስራ እድል በመፍጠር ሕይወታቸውን የሚለውጥ ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ተጠቃሚ የነበሩ ነዋሪዎች በበኩላቸው በቆይታቸው ሰርተው ካገኙት ገንዘብም ቆጥበው መለወጣቸውን ለአብነት አንስተዋል።
በዚህ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የ88 ከተሞች አመራሮች እና የሚመለከታቸው አካላት መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።