በቀዳማይ የልጅነት እድገት ፕሮግራም በ 3 አመት ውስጥ ከ 10 ሺ በላይ ህፃናት ተጠቃሚ ሆነዋል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing በቀዳማይ የልጅነት እድገት ፕሮግራም በ 3 አመት ውስጥ ከ 10 ሺ በላይ ህፃናት ተጠቃሚ ሆነዋል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN-የካቲት 12/2017 ዓ.ም

አዲስ አበባን በአፍሪካ ሕጻናትን ለማሳደግ ምቹና ምርጧ ከተማ ለማድረግ በቀዳማይ የልጅነት እድገት ፕሮግራም በ 3 አመት ውስጥ ከ 10 ሺ በላይ ህፃናት ተጠቃሚ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የ2017 ዓ.ም 4ኛ የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምክር ቤቱ ተገኝተው ባቀረቡት ሪፖርት በመዲናዋ የህፃናት፣ የሴቶች፣ የአረጋዊያን እና የአካል ጉዳተኞች መብትና ደህንነት ተጠብቆ የእኩል እድል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

11 ሺ 900 ነፍሰ-ጡር ሴቶች፣ አጥቢ እናቶችና ሕፃናት የቀጥታ የአልሚ ምግብ ድጋፍ እየተሰጠ ይገኛልም ብለዋል፡፡

በተቋቋሙ ከ900 በላይ የሚሆኑ ምቹ የሕፃናት መጫወቻና መዝናኛ ስፍራዎች እንዲሁም በሰንበት ዝግ መንገድ በርካታ ሕጻናት ተጠቃሚ መሆናቸውን አውስተዋል።

አረጋውያንን እና አካል ጉዳተኞችን በኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ በማህበራዊ ተካታችነትና የልማቱ ተሳታፊ በማድረግ ለ7 ሺ 591 አረጋውያን እና ለ1 ሺ 605 አካል ጉዳተኞች መሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎት፣ የስነ-ልቦና፣ የማህበራዊ እና የተሃድሶ አገልግሎቶች መሰጠቱን የገለጹት ከንቲባዋ ለ582 አካል ጉዳተኞች የሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ተደርጓልም ብለዋል።

የሴቶች ውሳኔ ሰጪነትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲሁም የማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭነት ለመቀነስ በሁሉም የከተማ አስተዳደሩ ስራዎች ውስጥ ታቅዶ መተግበሩን ጠቁመዋል፡፡

ለአብነትም በነገዋ የሴቶች ተሃድሶና የልቀት ማዕከል ለከፍተኛ ማህበራዊ ችግር የተጋለጡ 302 ሴቶች በመጀመሪያ ዙር ስልጠና ወስደው ስራ እንደተፈጠረላቸው አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም ማእከሉ በሁለተኛ ዙር 400 ሴቶችን ተቀብሎ በመረጡት ሙያ እያሰለጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በተማሪዎች እና በማህበረሰብ ምገባ ስራ 20 ሺህ የሚደርሱ ምንም ገቢ ያልነበራቸው እናቶችም የቋሚ የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ወጣቶችን በተመለከተም 1 ሺ 314 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በማልማትና ማስፋት ለበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉ ተመላክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review