በቀጣዮቹ ጊዜያት የትግራይን ህዝብ ልማት እና የለውጥ ፍላጎት የሚያሳኩ ተግባራት እንደሚከናወኑ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ገለጹ።
የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የፕሬዚዳንት ርክክብ ስነ ስርዓት ተካሂዷል።
በዚህም ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንትነትን ተረክበው የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር የተልዕኮ አፈጻጸም የቃል ኪዳን ሰነድን ፈርመዋል።
በሥነ-ስርዓቱም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ በዚሁ ወቅት፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያልተሰሩ በቀጣይ መሰራት ያለባቸው በርካታ ተግባራት አሉ ብለዋል።
ከፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም ጋር የተያያዘ ብቻም ሳይሆን የተፈጠሩ የጸጥታ፣ የፖለቲካ እንዲሁም የኢኮኖሚ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ ችግሮች ቀላል አለመሆናቸውን ገልጸው፤ በዚህ ላይ ለውጥ ለማምጣት በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በቀጣዮቹ ጊዜያት የትግራይን ህዝብ የልማት ጥያቄ እና የለውጥ ፍላጎት የሚያሳኩ ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
እንዲሁም የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር እንደሚሰራ እንዲሁም ያሉ ውጥረቶችን የማርገብ ስራ እንደሚከናወን አመልክተዋል።
የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት ለማሳካት የሚሰራበት መሆኑን ነው ያነሱት።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ስራዎችን መስራቱን ገልጸዋል።
ለአብነትም አገልግሎቶችን የመመለስ፣ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲሁም ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ መሰራቱን ገልጸው፤ ነገር ግን በቂ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
የፌዴራል መንግስት ለተጨማሪ አንድ ዓመት የጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲቀጥል ማድረጉ አዎንታዊ ተግባር መሆኑንም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የትግራይን የሰላም እና የለውጥ ፍላጎት ለማሳካት እና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በውስጥ የነበሩ የፖለቲካ ንትርኮች የፕሪቶሪያ ስምምነት በተሟላ መልኩ እንዳይከናወን በማድረግ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ አንስተዋል።
እርስ በእርስ በመጓተት መቀጠል እንደማይቻል የገለጹት አቶ ጌታቸው፥የተገኘውን ሰላም ለማደብዘዝ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን በመገንዘብ ሰላሙን ለማጽናት ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አሁን ላይ በትግራይ ህዝብ ዘንድ ያለው የሰላም እና የለውጥ ፍላጎት ሊቀለበስ የማይችል መሆኑን ገልጸዋል።
እነዚህን ከግምት በማስገባት የቀሩ ስራዎችን ማጠናቀቅ ስራ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ነው ያመላከቱት።