AMN- ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም
በቁጭት የጀመርነዉን የዓለም ከተሞች ከደረሱበት የመድረስ ግስጋሴያችን እንፈጥናለን እንጂ ፈፅሞ አንቆምም፤ አንዘገይምም ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራው የልኡካን ቡድን የማሌዢያ የአራት ቀናት ቆይታ ኳላ ላምፑር፣ ሳይበርጂያ እና ፑትራጂያ የተባሉ ከተሞቸን ጎብኝቷል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በቆይታችን ነባር ከተሞቻቸውን ከማደስ በተጨማሪ አዳዲስ ከተሞችንም እየገነቡ መሆኑን ተመልክተናል ሲሉ ገልጸዋል።
ነባሮቹም ሆኑ አዲስ የሚገነቡ ከተሞቻቸውን ልዩ የሚያደርጋቸው ነዋሪዎች እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸውና ጤናቸውን ለመጠበቅ የሚገለገሉባቸው ሰፋፊ የህዝብ መዝናኛዎችን፣ የኮንቬንሽንና የገበያ ማዕከላትን፣ መናፈሻዎችን እና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን መገንባታቸው ነው ሲሉም አመልክተዋል፡፡

ሰው ሰራሽ ወንዝ እና ሃይቆች በመፍጠር ንጹህ ምቹ እና ለኑሮ ተስማሚ የሆነ አካባቢን መገንባታቸው እንዲሁም ከአጠቃላይ የከተማው ስፋት 38 % የሚሆነውን ለአረንጓዴ ልማት በማዋል ትልቅ ስራ መስራታቸው ነው ሲሉም አክለዋል።
የሚገርመው ይህም በቂ አይደለም በማለት፣ ስራው እንደ ቅንጦት ሳይሆን ከመታመም በፊት መከላከል አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ እና የጤና አጠባበቅ ወሳኝ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ሰጥተው በመስራት ላይ ይገኛሉም ብለዋል።
በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ዘግይተንም ቢሆን የጀመርነው ስራ እየፈጠነ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
እኛ ከእነሱ አንፃር በተሻለ ሁኔታ ክረምትና በጋ ማሞቂያ እና ማቀዝቀዣ የማያስፈልገው፣ ወጥነት ያለው ተስማሚ የአየር ንብረት እና ውሃ፣ ትልቅ የሰው ሀይል እንዲሁም ሰፊ መሬት አለን ያሉት ከንቲባ አዳነችይህን እምቅ አቅማችንን በመጠቀም ከተማችንን ለመለወጥ በመስራት ላይ እንገኛለን በማለት ገልጸዋል።
በተለይ በአዲስ አበባ የአረንጓዴ ሽፋናችን በአምስት ዓመት ውስጥ ከነበረበት 2 ነጥብ 8 % ወደ 20 % ማድረስ ችለናል ሲሉም ገልጸዋል።
ህዝባችንን በማስተባበር በጀመርነው የ24/7 የስራ መርሃግብር የከተማችንን ነዋሪዎች ጤና ለመጠበቅ ወሳኝ የሆነውን ንጹህ እና ለኑሮ ተስማሚ የሆነ አካባቢ መፍጠርን፣ ነዋሪዎች እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸው ክፍት ቦታዎችን ማዘጋጀትን፣ ለእግረኛ መንገዶች ትኩረት በመስጠት ምቹና ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች መገንባትን፣ ፓርኮችን እና መናፈሻዎችን ማስፋፋትን፣ የአረንጏዴ ልማት ሽፋናችንን አሁን ካደረስነው በላይ ማሳደግን፣ የህፃናትና ታዳጊዎች የመጫወቻ ስፍራዎችን ማስፋፋትን እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን በብዛት መገንባትን አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል በማለት አስረድተዋል።
ብንዘገይም ገብቶን ጀምረናል፤ አካሄዳችን ትክክለኛ መሆኑንም ከኛ ቀድመው ከተገበሩት ጭምር ተመልክተናል ሲሉም ገልጸዋል በመልዕክታቸው።