በቡድን በመሆን የውንብድና ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ከነ ግብረ አበሮቻቸው በቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸው የለሚ ኩራ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገለፀ፡፡
ተከሳሾቹ የውንብድና ወንጀሉን የፈፀሙት በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ሰሚት ለሚ ኢንዱስትሪ ፖርክ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።
በአካባቢው ላይ አሽከርካሪዎች ልምምድ የሚያደርጉበትና የተለያዩ ግለሰቦች የሚዝናኑበት መሆኑን ሲያጤኑ የቆዩት ተከሳሾቹ በሽጉጥ በማስፈራራት፣ ጉዳት በማድረስና የያዙትን ንብረት በመቀማት ከአካባቢው ይሰወራሉ፡፡
እንደዚህ ዓይነት ወንጀሎች መፈፀማቸው ሪፖርት የደረሰው የአራብሳ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያም ባደረገው ብርቱ ክትትል አራት ተጠርጣሪዎችን ለወንጀል መፈፀሚያ ከሚጠቀሙበት ሽጉጥ ጋር በቁጥጥር አውሎአቸዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ የግል ተበዳዮች እንዲመርጧቸው በማድረግ በተሰራ ሰፊ የምርመራ ማስፋት ስራ የተሰረቁ ንብረቶችን በሰሌዳ ቁጥር ኮድ3 5616 አ/አ በሆነ ሞተር ሳይክል እየተንቀሳቀሱ የሚቀበሉ ተጨማሪ ሁለት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል የምርመራ መዝገብ በማደራጀት በዐቃቤ ህግ በኩልም ክስ እንዲመሰረትባቸው ተደርጓል፡፡
የተከሳሾቹ የክስ መዝገብ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለሚኩራ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ እየታየ ሲሆን በማረሚያ ቤት ሆነውም ጉዳያቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኝም ጭምር ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ወንጀሉ በተፈፀመበት አካባቢ ተጠርጣሪዎቹ የወንጀል ድርጊቱን ሲፈፅሙ አንዳንድ ሰዎች ቆመው ሲመለከቱ እንደነበረ ያስታወሰው ፖሊስ ህብረተሰቡ ወንጀል እየተፈፀመ እያየ ለፖሊስ መረጃ አለመስጠቱ ወይም እየተፈፀመ ያለን ወንጀል እንዲቋረጥ አለማድረግ በህግ ተጠያቂ ሊያርገው እንደሚችል በመገንዘብ ተገቢውን ትብብር ማድረግ እንደሚገባው ፖሊስ ማሳሰቡን ከከተማዉ ፖሊስ ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል፡፡