AMN – የካቲት- 6/2017 ዓ.ም
በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎች እና ውሳኔዎች ግባቸውን እንዲመቱ የፌዴራል ተቋማት ብልጽግና አደረጃጀት አባላት ሚና የላቀ መሆኑን የፓርቲው ምክር ቤት አባልና የፌዴራል ተቋማት ብልጽግና አደረጃጀት ሰብሳቢ አለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ።
በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ የፌዴራል ተቋማት ብልጽግና አደረጃጀት አባላት ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
ውይይቱ በፓርቲው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ ወጥ የሆነ ግንዛቤ በመያዝ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲከወኑ ለማድረግ ያለመ መሆኑም ተገልጿል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የፌዴራል ተቋማት ብልጽግና አደረጃጀት ሰብሳቢ አለሙ ስሜ(ዶ/ር) እንዳሉት ጉባኤው በሁሉም መስክ ስኬታማ ሆኖ ተጠናቋል።
በፓርቲው የመጀመሪያው ጉባኤ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ስኬታማ ሆነው መፈጸማቸውን በሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ መገምገሙን አንስተዋል፡፡
ለዚህም የፌዴራል ተቋማት ብልጽግና አደረጃጀት ሚና አወንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸው፤ በሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ የተቀመጡ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችም ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲተገበሩ የአባላቱ ሚና ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

ውሳኔዎችና አቅጣጫዎቹ በፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውስጥ ተካተው መተግበር እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ለዚህም ተቋማት ከያዙት ዕቅዶች ጋር በተናበበ መልኩ ለመተግበር መስራት እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
በውሳኔና አቅጣጫዎች ላይ የመንግሥት ሰራተኞችና ህዝቡ ግንዛቤ እንዲጨብጥ በማድረግ ለሀገራዊ ግቦች ስኬት በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የፌዴራል ተቋማት ብልጽግና አደረጃጀት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ተስፋዬ ቤልጂጌ(ዶ/ር) በበኩላቸው በውሳኔ እና አቅጣጫዎች ላይ አመራሩ ወጥ የሆነ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል ብለዋል፡፡
የፓርቲው አመራር እና አባላትን ብቃትና ጥራት በማሳደግ ጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ስራውን ማጠናከር፣ ብሄራዊነት ገዥ ትርክት እንዲሆን መስራት፣ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታን ጨምሮ ስምንት አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ጠቅሰዋል።
የጉባኤው ውሳኔዎች እስከታች መውረድ እንዳለበት ገልጸው፤ ለዚህም ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚጠበቅበት አጽንኦት መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።