AMN-ጥር 15/2017 ዓ.ም
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተጀመሩ አዳዲስ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ በጥሩ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ።
ዶክተር ዓለሙ ስሜ በብልጽግና ፓርቲ አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ለመተግበር ቃል በተገባው መሰረት በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራትና የተገኙ ውጤቶችን በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ባለፉት ስድስት ዓመታት በዘርፉ የተደረጉ የለውጥ ሥራዎች የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና ዘርፈ ብዙ ስኬቶች የተመዘገቡበት መሆኑን አንስተዋል።
የግል ባለኃብቶች በትናንሽ አውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ በመንግሥት የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ የግንባታ ቦታዎችን የመለየትና ወደ ስራ ለማስገባት የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በተለይም በአየርና በየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት የተያዙ ግቦች አፈጻጸም የተሳካ መሆኑን ጠቅሰው አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን በማዘመንና ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ የተለያዩ አሰራሮች ተዘርግተው ተግባራዊ መደረጋቸውን ጠቅሰው በዚህም ጥሩ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
በስድስት የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተጀመሩ አዳዲስ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታዎች በጥሩ አፈፃፀም ደረጃ ላይ መሆናቸውን ሚኒስተሩ ተናግረዋል።
የግሉን ዘርፍ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ማሳተፍ የሚያስችሉ አሰራሮችና የማበረታቻ ማዕቀፍ መዘርጋቱን ጠቅሰው ይህም በርካታ ባለኃብትን እየሳበ መሆኑን አንስተዋል።
በትናንሽ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የግል ባለሃብቶች እንዲሳተፉ መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በዘርፉ ለመሳተፍ ጥያቄ ያቀረቡ መኖራቸውንም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
ለዚህም ቦታዎችን በመለየት እንዲሁም በግንባታው ለሚሳተፉ ባለኃብቶች የቴክኒክ ድጋፍ የመስጠትና ወደ ሥራ ለማስገባት የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የአየር ትራንስፖርት ደህንነትን አስተማማኝ ከማድረግ አኳያም የአቪየሽን ዘርፉን በሁሉም ረገድ የማዘመንና የማጠናከር ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
በለውጡ ስድስት ዓመታት የአዳዲስ አውሮፕላኖች ግዥ በመፈፀምና ወደ ስራ በማስገባት በዘርፉ አገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ የላቀ ውጤት መመዝገቡንም ገልጸዋል።
ከሎጂስቲክስ ጋር በተያያዘ ኢኮኖሚውን ማሳለጥ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ ለአብነትም የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ግንባታ 80 በመቶ መድረሱን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ማቆያ መሰረተ ልማት ግንባታም በሂደት ላይ መሆኑን ነው ያስረዱት።
ለባህር አገልግሎት መሳለጥ የአንድ መርከብ ግዥ መፈፀሙን ጠቅሰው የባቡር አገልግሎትን ለማሳደግም በስድስት ዓመታት የ200 ዋገኖች ግዥ ተከናውኗል ብለዋል።
የየብስ ትራንስፖርት ተደራሽነትን ለማሳደግም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመንገድ ግንባታዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት።