በተለያዩ ጣዕሞች የቀረቡ የትምባሆ ውጤቶች ወጣቶችን ለሱስ እና ለሞት እየዳረጉ ነው-የዓለም ጤና ድርጅት

  • Post category:ጤና

AMN-ግንቦት 23/2017 ዓ.ም

በተለያዩ ጣዕሞች የቀረቡ የትምባሆ ውጤቶች ወጣቶችን ለሱስ እና ለሞት እየዳረጉ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት ዛሬ እየተከበረ የሚገኘውን የዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን በማስመልከት ባወጣው ሪፖርት፤ ሀገራት ወጣቶችን ከሱስ ከበሽታ እና ከሞት ለመጠበቅ ሲባል ትምባሆ እና የኒኮቲን ምርቶችን ሊያግዱ እንደሚገባ ገልጿል፡፡

በተለይም ‘ኢ-ሲጋሬት’ የተባለው እና በተለያየ ጣፋጭ ከረሜላ መልክ የሚዘጋጁ የትምባሆ ምርቶች ወጣቶችን ተጋላጭ እያደረጉ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ይህም ሱሱን በቀላሉ ለማቆም አዳጋች ከማድረጉ ባለፈ ለከባድ የሳንባ በሽታ የሚያጋልጥ ነው ተብሏል፡፡

ከትምባሆ ተጠቃሚዎች መካከል ግማሽ የሚያህሉት ሕይወታቸውን የሚያጡት በተለያዩ ጣዕሞች በቀረቡ የትምባሆ ምርቶች መሆኑም ተገልጿል፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሐኖም ፤ ጣዕም ያላቸው የትምባሆ ምርቶች አዲስ የሱስ ማዕበልን እያስፋፉ በመሆኑ ሊታገዱ ይገባል ብለዋል፡፡

በትምባሆ ምክንያት በየዓመቱ ከ8 ሚልዮን በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ሀገራት ቆራጥ ርምጃ እንዲወስዱም ጠይቀዋል፡፡

ወጣቶች ወደ ትምባሆ እና ኒኮቲን ምርቶች እንዲሳቡ የሚያደርጋቸው ዋነኛው ምክንያት በተለያየ ጣዕም መቅርቡ መሆኑንም አፍሪካ ኒውስ አስነብቧል።

የዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን በየዓመቱ ግንቦት 23 (May 31) የሚከበር ሲሆን ዘንድሮም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ38ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ “በትምባሆና በኒኮቲን ምርቶች ላይ የትምባሆ ኢንዱስትሪ አሳሳችና ድብቅ ስልቶችን በማጋለጥ ወጣቶችን እንታደግ!” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review