“በተሳሳተ መንገድ ወደ ትጥቅ ትግል ገብተን ባደረስነው በደል ህዝባችን ለመካስ ዝግጁ ነን።” የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂ ሃይሎች

You are currently viewing “በተሳሳተ መንገድ ወደ ትጥቅ ትግል ገብተን ባደረስነው በደል ህዝባችን ለመካስ ዝግጁ ነን።” የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂ ሃይሎች

AMN – ታኅሣሥ 20/2017 ዓ.ም

በተሳሳተ መንገድ ወደ ትጥቅ ትግል ገብተን ባደረስነው በደል ህዝባችን ለመካስ ዝግጁ ነን ሲሉ የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂ ሃይሎች ገለጹ፡፡

በምስራቅ አማራ ቀጠና አካባቢ የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ የታጣቂ ቡድኑ አባላት የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ተዘጋጀላቸው የተሃድሶ ማሰልጠኛ ማዕከል ገብተዋል።

በአማራ ክልል የሰላም መደፍረስ ከተከሰተ ከአንድ ዓመት በላይ ዘልቋል። ይህንን ግጭት ለማስቆምም መንግስት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን በመቀበል እጃቸውን ለመንግስት እየሰጡ ይገኛሉ።

በዛሬው እለትም በምስራቅ አማራ ቀጠና ማለትም በዋግኽምራ ብሔረሰብ፣ በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ወሎ፣ በደሴ ከተማ፣ በኮምቦልቻ ከተማ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ የታጣቂ ቡድኑ አባላት መንግስት ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ተሀድሶ ማሰልጠኛው ማዕከል ገብተዋል።

ምንም እንኳ መመለስ የሚገባቸው የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ቢኖሩም ለማስመለስ የሄድንበት መንገድ የተሳሳተ ነው ያሉት ተመላሽ የታጣቂ ቡድኑ አባላት፤ የሕዝብ ጥያቄ እናስመልሳለን ብለን ጫካ ከገባን በኋላ የፈጸምነውን ድርጊት ስናስበው የተሳሳተ መንገድ እንደተከተልንና ሕዝቡ ላይ የከፋ በደል እንዳደረስን ተፀፅተናል ብለዋል።

በመሆኑም የበደልነውን ህዝብ ለመካስ መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለን መጥተናል ሲሉ አመልክተዋል።

ሌሎች ጫካ የሚገኙ ወንድሞቻችንም የተሰለፉበት ዓላማ የተሳሳተና ሀገርና ሕዝቡን የሚጎዳ መሆኑን ተገንዝበው የመንግስትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምስራቅ እዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ምክትል አዛዠ ኮሎኔል ወንድየ መንገሻ የሰላም እጦት ሕዝብን እና ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን በመገንዘብ ሌሎች ጫካ የገቡ ታጣቂዎችም የነዚህን አርዕያ በመከተል የሰላምን አማራጭ እንዲከተሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የሰላምን ጥሪ ተቀብለው ለሚመጡት የታጣቂ ቡድኑ አባላት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አመራሮች እና ሌሎች እንግዶች መልካም አቀባበል እንዳደረጉላቸው መገለጹን ከአማራ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review