በተግባር የተገለጠ ቃል

You are currently viewing በተግባር የተገለጠ ቃል

የኮሪደር ልማቱ ካዛንቺስን የመሳሰሉ የመዲናዋ አካባቢዎችን ውብ በማድረግ  አዲስ አበባ የዘመናዊ ከተማ ገፅታን እንድትላበስ አድርጓታል

አዲስ አበባ ጥንታዊ ከተማ ናት። ከተማዋ በኢትዮጵያውያን አቅም፣ ጉልበትና ገንዘብ እንዲሁም የምህንድስና ጥበብ የተዋበች የአፍሪካ መዲና ናት። የኢትዮጵያ የስልጣኔ  ፀሐይ መውጫ ምስራቅ፣ መቋደሻም ናት ይህች ከተማ፡፡

ከተማዋ በእድሜዋ ጅረት ውስጥ ራሷን እያዘመነች ከመሄድ አንፃር ሰፊ ጉድለት እንደሚታይባት ገፅታዋ ምስክር ሆኖ የሚቀርብ ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ ነዋሪዎቿ በየጊዜው ለጎርፍ እና ለእሳት አደጋዎች አብዝተው የሚጋለጡባት፣ በቆሻሻ ምክንያት ለሚከሰቱ ወረርሽኞች እጅ የሚሰጡባት፣ ከመኪና ጋር እየተጋፉ የሚሄዱባት፣ ማገራቸው ባዘመመ እና ጣሪያቸው ባረጀ ቤት የሚኖሩባት፣ መፀዳጃ ቤት በወረፋ የሚጠቀሙባት፣ ፀሐይ ስትጠልቅ በጨለማ፤ ክረምት ሲገባ በጎርፍ የሚዋጡባት ከተማ እንደነበረች መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አይተንና ሰምተንም የታዝብነው እውነት ነው፡፡

ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ትዕግስቱ ይመር እንደሚሉት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በነዋሪዎቹ ተደጋግመው ይነሱ የነበሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በፍጥነትና ዘላቂነት ባለው መልኩ እየተፈቱ መጥተዋል፡፡ በተለይም በኮሪደር ልማቱ እየመጣ ባለው ለውጥ አብዛኛዎቹ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ ሲሆን፣ ልማቱ እየሰፋ ሲመጣም በርካታ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮችን መቅረፍ ያስችላል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባሳለፍነው ረቡዕ አድርጎ ነበር፡፡ በዚህ ወቅትም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የኮሪደር ልማቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ ከተማዋን በመሰረታዊነት እያደሰ ይገኛል ብለዋል።

በኮሪደር ልማት የመጣው ለውጥ “አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ እናደርጋታለን” በሚል ለህዝቡ ከተገባው ቃል የመነጨ ነው። ለአብነት የኮሪደር ልማት ስራው የከተማዋ የመንገድ መሰረተ ልማት እና የአረንጓዴ ልማት ሽፋን እጅግ ከፍ እንዲል  አስችሏል፡፡ ይህም ለከተማዋ ነዋሪዎች ጤና ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑን ሁሉም የሚገነዘበው ጉዳይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

አክለውም በኮሪደር ልማቱ የመኪና መንገድ ብቻ ሳይሆን ተሽከርካሪ የሌላቸው ከ80 በመቶ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች በቀላሉ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ የእግረኛ መንገዶች ሰፍተዋል፤ የሳይክል መንገዶችንም ማስፋፋት በመጀመሩ ህዝቡ ተጠቃሚ ሆኗል።

በከተማዋ በተለምዶ ሲ.ኤም.ሲ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በኮሪደር ልማቱ በተሰራው  የሳይክል መንገድ ላይ እየተጠቀሙ ካገኘናቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ሳሙኤል ባዩ አንዱ ነው፡፡ ወጣቱ እንደተናገረው፣ የኮሪደር ልማቱ ይዞት በመጣው በረከት የመዲናዋ ነዋሪ እየተጠቀመ ነው፡፡ “አሁን በነፃነት ከፈለግን በግር አሊያም በሳይክል የምንቀሳቀስባቸው፣ ሲደክመንም አረፍ የምንልባቸው እንዲሁም የተለያዩ ምግብና መጠጦችን በአቅራቢያችን እየተዝናናን የምንጠቀምባቸው ስፍራዎች ተገንብተዋል”  ብሏል፡፡

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የኮሪደር ልማቱን አስመልክቶ ለምክር ቤት አባላቱ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ እንደገለፁት- ኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገፅታ መቀየሩ እና ለህዝቡ ምቹ መኖሪያ እንድትሆን ከማድረጉ ጎን ለጎን ለበርካታ ወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድልም ፈጥሯል፡፡

ይህንንም አስመልክቶ የዝግጅት ክፍላችን በአራት ኪሎ አካባቢ በኮሪደር ልማት ላይ ከተሰማሩ የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት አዲሱ ጌታው እና ወጣት ሱራፌል በደዊ ጋር ቆይታ አድርጎ ነበር። ወጣቶቹ በኮሪደር ልማቱ የስራ ዕድል ማግኘታቸውን እና ከተማቸውን እያለሙ በመጠቀማቸውም ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀውልናል፡፡  የዝግጅት ክፍላችንም በኮሪደር ልማቱ እየተሳተፉ ያሉ ዜጎች በከፍተኛ መነቃቃትና ትብብር ስራቸውን በፍጥነትና በጥራት እያከናወኑ እንደሆነ በምልከታው አስተውሏል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ትዕግስቱ ይመር በበኩላቸው፣ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ “‘አዲስ አበባን አዲስም አበባም’ እናደርጋታለን” በሚል መርህ በኮሪደር ልማት እየመጣ ባለው አስደማሚ ለውጥ ከተማዋ በርግጥም አዲስም፣ አበባም እየሆነች ነው ብለዋል፡፡

በርካታ በተጎሳቆሉ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ቤታቸው ታድሶ አሊያም ወደ ምቹ ስፍራ ተዘዋውረው እየኖሩ ነው፡፡ የተጨናነቁ መንገዶች ሰፋ ሰፋ ብለዋል፡፡ በተለያዩ ስፍራዎች የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ የህፃናት  መጫዎቻዎች፣ በርካታ የህዝብ መናፈሻዎች፣ ከዘመኑ ጋር የተወዳጁ የንግድ ቤቶች እና መሰል የከተማዋን ምጣኔ ሀብት ከፍ በማድረግ ህዝቡን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

ለአብነትም ከሰሞኑ በካዛንቺስ አካባቢ በፍጥነትና በጥራት የተከናወነው የኮሪደር ልማት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ተመርቆ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህ የካዛንቺስ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት ስራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሁለተኛ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት አካል እንደሆነም ይታወቃል።

በሌላ በኩልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በ 21 ሄክታር ላይ የተገነባውን የቡልቡላ ፓርክ እና ከቦሌ ካርጎ እስከ አቃቂ ድልድይ ድረስ 14 ኪሎ ሜትር ላይ ያለው የአረንጓዴ ልማት ስራም ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡

ይህ ስፍራ ከዚህ ቀደም ለእይታ የማይመች፣ እጅግ ቆሽሾ የነበረ እና ማንም መለስ ብሎ አይቶት የማያውቀው ነበር። አሁን አካባቢው ወደ ሀብትነት፣ ትልቅ መዝናኛ እና የህዝብ መዋያና መናፈሻነት መቀየር መቻሉ ደስ እንደሚያሰኝ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ይህንን አስመልክቶ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የከተማ ልማት ባለሙያና አማካሪ ኢንጂኒየር በሱፈቃድ ጌታቸው እንደሚሉት የኮሪደር ልማቱ ካዛንቺስን የመሳሰሉ የመዲናዋ አካባቢዎችን ውብ በማድረግ አዲስ አበባ የዘመናዊ ከተማ ገፅታን እንድትላበስ አድርጓታል፡፡

እነዚህ  ሀሴትን የሚያጎናፅፉ የልማት ስራዎች ከተማዋን ከዓለማችን ፅዱ፣ ውብና ተመራጭ ከተሞች ተርታ የሚያሰልፉ ነው፡፡ በተለይም ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ደስተኛ ሕይወትን እንዲመሩ የሚያስችሉ ስለመሆናቸውም ጠቁመዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ሁሉን ያቀናጀ የከተማ ግንባታ (smart city) አካል በመሆኑ ለዘመናዊ ከተማ ግንባታ እንደ ሀገርም ሞዴል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የሰውና የተሽከርካሪ መጓጓዣ መንገዶችን፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፤ የመብራት፣ የስልክ እና ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች፣ የመዝናኛና የማረፊያ ቦታዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሰፍራዎች እና መሰል የማህበረሰቡን ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ መሆናቸው ደግሞ ስራውን የሚደነቅ ያደርገዋል፡፡ በተለይም በልማቱ ከቦታቸው የሚነሱ ነዋሪዎች የሚዛወሩባቸው  ዘመናዊ  የመኖሪያ መንደሮችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ደግሞ በጉልህ የሚታይ ትልቅ ተግባር ነው ብለዋል የከተማ ልማት ባለሙያው ኢንጂኒየር በሱፈቃድ ጌታቸው፡፡

የካዛንቺስ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት ስራ የልማት ተነሽዎች ከተዘዋወሩበት አካባቢ የገላን ጉራ አዲስ መንደር አንዱ ነው፡፡ ይህ ውብ፣ ያሸበረቀና ለኑሮ ተስማሚ ተደርጎ የተገነባው ስፍራ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ይገኛል፡፡ በዚህ መንደር ነዋሪ ከሆኑት መካከል የአራት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ከበቡሽ ለሞሎ አንዷ ናቸው። ቀድሞ በነበሩበት ካዛንቺስ አከባቢ ምንም አይነት ገቢ የሚያገኙበት ሥራ እንዳልነበራቸው ያስታውሳሉ፡፡

አሁን ግን በሚኖሩበት አዲስ መንደር የተመቻቸ መኖሪያ ቤት ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸው በእጅጉ እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ፡፡ እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ እናቶች በገላን ጉራ የእንጀራ ማዕከል የስራ ዕድል ማግኘታቸው የነበረባቸውን ጭንቀት እንዳስወገደው ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል፡፡

“በአዳጊ ሀገራት የከተሞች መስፋፋትና ፈተናዎቻቸው”  (THE CHALLENGES OF URBANIZATION IN DEVELOPING COUNTRIES) በሚል ርዕስ ኖህ ሉሙን አባንያም እና ኤድዌ ዳንካኖ በግሎባል ጆርናል ኦቭ አፕላይድ፣ ማኔጅመንት እና ሶሻል ሳይንሶች ላይ ባሳተሙት ጥናታቸው እንደገለፁት፣ በአዳጊ ሀገራት ባሉ ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች ከፍተኛ የህዝብ ጥግግት፣ በቂ ያልሆነ መሠረተ ልማት፣ የተመጣጣኝ መኖሪያ ቤት እጦት፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ብክለት እና የመሳሰሉ ችግሮች እያጋጠሟቸው ነው፡፡ ይህም  ዘመኑን ያልዋጀ ልማትና ደካማ የከተማ ፕላን በመከተላቸው የመጣ ነው፡፡

ጥናቱ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የከተሞች መስፋፋት ከማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ተግዳሮቶች ጋር የተቆራኘ መሆኑን ያመላከተ ሲሆን፣ እነዚህም ድህነት፣ ስራ አጥነት፣ ከፍተኛ የአደጋ ተጋላጭነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ መጨናነቅ እና የኢንዱስትሪ ቆሻሻን በህገ ወጥ መንገድ መልቀቅ፣ የመጸዳጃ ቤቶች ውስንነት፣ የንፅህና ጉድለት፣ የትራፊክ መጨናነቅ እና የወንዞች ብክለትን የመሳሰሉት ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከላይ በጥናት የተመላከቱትን  ችግሮች በዘላቂነት እየፈታ ያለ፣ ከተማዋን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ ያደረገ፣ የነዋሪዎቿን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችንም በመሰረታዊነት እየቀረፈ እንደሆነም የከተማ ልማት ባለሙያው ኢንጂኒየር በሱፈቃድ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

ባሳለፍነው ረቡዕ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባ በተከናወነበት ወቅት የምክር ቤት አባላት የማህበረሰቡን አስተያየትና ጥያቄዎች ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡ ለአብነትም በኮሪደር ልማት፣ በመልሶ ማልማት እና በወንዞች ዳርቻዎች ልማት አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን እውን ለማድረግ በታቀደው መሰረት ለወጣቶች እና ለሴቶች ሰፋፊ የስራ ዕድሎች መፈጠራቸውን አንስተዋል።

የሰው ተኮር ስራዎች በተለይም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ያሉ ዜጎች የከተማ አስተዳደሩ ከሚያመነጨው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻለ ከመሆኑም በላይ ህዝቡም ተገቢውን እውቅና እየሰጠ ይገኛልም ብለዋል።

በሌላ በኩልም አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የውሃ ስርጭት፣ የመብራት፣ የመንገድና መሰል   ችግሮች እንዲፈቱ በሚወክሏቸው የከተማዋ ነዋሪዎች አማካኝነት መጠየቃቸውን የገለፁት የምክር ቤት አባላቱ፣ በተለይም ይህንን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል የኮሪደር ልማቱ ያልደረሰባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ እኛም ይምጣልን ጥያቄ እንዳነሱም ጠቁመዋል፡፡

ይህንን አስመልክቶ ምላሽ የሰጡት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የከተማዋ ነዋሪዎች ልማቱ ወደ ሁሉም የከተማችን አካባቢዎች እንዲመጣ መጠየቃቸው አግባብነት ያለው ጥያቄ ነው፡፡ ቢሆንም ስራው ሰፊ ሀብት እና ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ በጥናት እና በቅደም ተከተል ወደ ሁሉም የከተማዋ ክፍሎች በመምጣት የምናለማ ይሆናል ብለዋል፡፡

ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የከተማ ልማትና የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም የኮሪደር ልማቱ በሁሉም ከተማዋ ክፍል እየሰፋ ሲሄድ የነዋሪዎቹ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊና መሰል ችግሮች በዘላቂነት የሚፈቱበትን ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review