ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከመላው ሀገሪቱ ከተውጣጡ የንግዱ ማህበረሰብ ጋር ተወያይተዋል፡፡
የንግዱ ማህበረሰብ አባላትም ከአገልግሎት አሰጣጥ፤ ከግብርና ታክስ አከፋፈል፤ ከነዳጅና ፋይናንስ አቅርቦት፤ ከህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ጋር የተያያዙ ጥያቄና አስተያየቶችን አቅርበዋል፡፡
ተሳታፊዎቹ በተጨማሪም ከመሰረተ ልማት ግንባታ፤ ከግብአት አቅርቦት፤ የሃገር ዉስጥ ምርት ከመጠቀም ፤ ከዲፕሎማሲና መሰል ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ሃሳብና ጥያቄዎችንም አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተሳታፊዎቹ ላነሷቸዉ አስተያየትና ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዪ ችግሮችን ለመቅረፍ የመሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎትን አስጀምረናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
አብዛኛውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ወደዚህ የዘመነ አሰራር እየገባ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብዛኛውን አገልግሎት ቨርቿል በማድረግ የስራ አፈፃፀምን ለመጨመርና ሌብነትን ለመቀነስ መታቀዱን አስረድተዋል።
አብዛኛዎቹ ዋና ዋና ከተሞች ወደዚህ የዘመነ አሰራር ለመግባት እየተዘጋጁ መሆናቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን አይነት አገልግሎት አሰጣጥ በሃገሪቱ ለማስፋፋት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለሟሟላት ዜጋው ግብሩን መክፈል እንዳለበት አመላክተዋል።
መንግስት የሚያገኘውን ገቢ 100 በመቶ ኢትዮጵያ ላይ እንደሚያውል የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተገናኘ በተለያዩ ቦታዎች የሚታየውን የጥቃቅን ሙስና ጉዳይ በማንሳት ተገልጋዩም ለዚህ ችግር 50 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ እንደሚወስድ አስረድተዋል።
ሁሉም በሃቀኝነት ቢያገለግል ድህነትን መስበር እንችላለን ብለዋል፡፡
በሊያት ካሰሁን