በትውልድ ቅብብሎሽ የጎለበተው የፖሊስ ሰራዊት

You are currently viewing በትውልድ ቅብብሎሽ የጎለበተው የፖሊስ ሰራዊት

ኅብረ-ብሔራዊነቱን የጠበቀ የፖሊስ ሰራዊት ተገንብቷል

ፖሊስ በአንድ ሀገር ሰላምና ደህንነትን በማስጠበቅ ቁልፍ ሚና ከሚጫወቱ የፀጥታ አካላት አንዱ ነው፡፡ ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል፣ ሲፈፀምም ወንጀለኞችን ለህግ በማቅረብ ህግና ስርዓት በማስከበር ትልቅ ሚና ይጫወታል። የኢትዮጵያ ፖሊስ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዋጅ የተቋቋመው ሚያዝያ 29 ቀን 1901 ዓ.ም ነው፡፡ አሁን 116 ዓመት ያስቆጠረ አንጋፋ ተቋም ነው፡፡

116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ብሔራዊ ቀን፣ “የተለወጠ ፖሊስ እየተለወጠ ላለ ሀገር!” በሚል መሪ ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡ ከትናንት በስቲያም በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም የፖሊስ ቀንና አውደ-ርዕይ ተከፍቷል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ፖሊስ ከተመሰረተበት 1901 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ያለው የፖሊስ ታሪክ በተለያየ መልኩ በመዘከር ላይ ነው፡፡ 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘው ተሻገር የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በትውልድ ቅብብሎሽ የተገነባ ሰራዊትና ተቋም ነው፡፡ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በተሰሩ የሪፎርም ስራዎች የሰራዊቱ አቅም እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

“የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአመለካከቱ የተስተካከለና የፓርቲ ውግንና የሌለው እንዲሆን ተደርጎ የተቀረፀበት መንገድ የሚያስገርም ነው፡፡ ሰራዊቱ አቅሙ በየጊዜው እያደገ መጥቷል፡፡ የሀገራችን የተቋም ግንባታ ስራ ላይ ስንነጋገር ተቋም ተገንብቷል ብለን ምስክርነት እንስጥ ቢባል፣ በተጨባጭ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስን ልንጠቅስ የምንችለው፡፡”

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ባደረገው ውጤታማ ሪፎርም ከሀገር አልፎ በጂቡቲ፣ ቻይና እና በተለያዩ ሀገራት ሽልማቶችን እያገኘ ነው፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ስሙ በክፉ ይነሳ የነበረው የፌዴራል ፖሊስ፣ ዛሬ በቴክኖሎጂ አቅሙ፣ የወንጀል ምርመራን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በማከናወን፣ በሰው ሃብት ልማት የሚጠቀስ ተቋም ሆኗል ነው ያሉት አፈ- ጉባኤ አገኘው ተሻገር፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በማቀፍ ኅብረ-ብሔራዊነቱን  የጠበቀ ተቋም ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስን አቅም ለማሳደግ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ያነሱት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው፣ የወንጀል ምርመራ ሰብዓዊ መብትን ያከበረ፣ በህግና ስርዓት የሚሰራ፣ የሙያ ብቃት ያለው፣ በቴክኒክና ታክቲክ የተደራጀ እንዲሆን በመሰራቱ፣ ከለውጡ በፊት ፖሊስ ይወቀስበት የነበረውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በሪፎርሙ በመቀየር አሁን ላይ በሀገራችን፣ በቀጣናውና በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተቋማት ጭምር ክብርና ተቀባይነትን ያገኘ ተቋም ሆኗል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከአጋር የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ሀገርን ማፅናት መቻሉን የጠቆሙት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ፣ ፖሊስ አገልጋይነቱን ይበልጥ በማስቀጠል ከሀገራችን፣ ከቀጣናውና ከአህጉር አቀፍ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሰራልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነቱን የጠበቀ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተቋም መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ረዳት ኮሚሽነር ሞገስ ቸኮል ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ማህበረሰብ አቀፍና መረጃ መር ሞዴልን በመከተል ይሰራል። በፖሊስ ላይ በተሰራው ሪፎርም ከማህበረሰቡ ጋር ተቀራርቦ አብሮ በመስራት ያለው አመኔታ ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡

የተቀናጀ የኮማንድ ማዕከል በማቋቋም፣ ህብረተሰቡ የሚያየውን ወንጀል በቀጥታ ለፌዴራል ፖሊስ ጥቆማ የሚሰጥበት መተግበሪያ በልፅጎ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፣ ፖሊስ የሚደርሰውን መረጃ በመንተራስ ፈጣን ምላሽ እየሰጠ ይገኛል። በዚህ ዓይነቱ ተግባርም የፌዴራል ፖሊስ በአፍሪካ የመጀመሪያው መሆኑን ረዳት ኮሚሽነር ሞገስ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀልን ለመከላከል የድሮን ቴክኖሎጂንና ዘመናዊ ተሽከርካሪና ትጥቆችን ታጥቋል፡፡ በሰው ኃይል ልማት ረገድም አመራሩና ሰራዊቱ ወቅቱ የሚጠይቀው ወንጀልን የመከላከል የፖሊስ ቁመና ላይ እንዲደርስ በስልጠና እንዲበቃ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ከፌዴራል እና ክልል የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር በመላው ሀገሪቱ ስምሪት ወስዶ እየሰራ ይገኛል። የፌዴራል መንግስት ተቋማትንና ጥቅሞችን በመጠበቅ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ ሊቃጡ የሚችሉ የሽብርተኝነት፣ የፀረ ሰላምና ፅንፈኝነት እንቅስቃሴዎችን በመከላከል የተሻለ ወንጀልን የመከላከል አቅም ላይ ይገኛል፡፡

በበዓሉ ላይ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጀነራል እና ጀነራል መኮንኖች፣ የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሎች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ አባት አርበኞች፣ የቀድሞ የፖሊስ ሠራዊት አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ከሚያዚያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት እየተካሄደ ባለው ሲምፖዚየም እና አወደ ርዕይ፣ የኢትዮጵያን ፖሊስ ታሪካዊ አመጣጥና የተመዘገቡ ፖሊሳዊ የሪፎርም ስኬቶችን የሚያሳዩ፣ የኢትዮጵያን የፖሊስ ታሪክ፣ የፖሊስ ሪፎርም፣ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ፣ የወንጀል መከላከል፣ የወንጀል ምርመራ፣ የሠራዊት ግንባታ፣ በፖሊሳዊ ቴክኖሎጂ፣ ጤና አገልግሎት፣ የጀግኖች ማዕከል፣ አዲሱ የፌዴራል ፖሊስ የደንብ ልብስን ጨምሮ ተቋማዊ የምርታማነትና የለውጥ እርምጃዎች በማካተት ለዕይታ ቀርበው እየተጎበኙ ይገኛሉ።

ፖሊስ የደረሰበት የእድገት ደረጃ፣ አሁናዊ ቁመናና ቀጣይ አካሄድ በሚያሳይ መልኩም በመጪው ሚያዝያ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በታላቅ ድምቀት በዓሉ ይከበራል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review