AMN-የካቲት 28/2017 ዓ.ም
በትግራይ ክልል አዲሱ ስርዓተ ትምህርትን በተሟላ መንገድ ወደ ሥራ ለማስገባት ተጨማሪ የመፅሃፍት ህትመት ዝግጅት መጠናቀቁ ተገልጿል።
በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኪዳነማርያም ወልደሚካኤል እንደገለፁት፣ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ለ13 የትምህርት ዓይነቶች የመማሪያ መፅሃፍት ህትመት ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቋል።
በዚህም የትምህርት ሚኒስቴር እና ዩኒሴፍ በጋራ የ20 ሚሊየን ቅጂ ተጨማሪ የመማሪያ መፅሀፍት ህትመት ለማከናወን የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል።
እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን መፅሃፍቱን በማሰራጨት አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በክልሉ በተሟላ መንገድ ተግባራዊ ይደረጋል።
ሚኒስቴሩ ለመፅሃፍት ህትመትና ለመምህራን አቅም ግንባታ የበጀት ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ 650 ሺህ የሚሆኑ የመማሪያ መፅሃፍትን ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ማስረከቡን አቶ ኪዳነማሪያም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።