በቻይና ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ የሚያስችል ዲጂታል ፓቪሊዮን ተመርቆ ስራ ጀመረ

AMN-ጥር 12/2017 ዓ.ም

በቻይና የሚገኙ ሶስት የኦን ላይን ፕላትፎርሞች ላይ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንትና ንግድ እድሎች እንዲሁም የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅና ለመሸጥ የሚያስችል ዲጂታል ፓቪሊዮን ይፋዊ ማስጀመሪያ መርኃ- ግብር በቤጂንግ የኢፌዲሪ ኤምባሲ ተካሄዷል፡፡

የፓቪሊዮን ማስጀመሪያ መርኃ-ግብሩ የኢትዮጵያን የቢዝነስ አማራጮችና ቱሪዝም መዳረሻዎችን በቻይና የበለጠ ለማስተዋወቅ እንዲቻል በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራ ላይ ከተሰማራው “ግራንድ ወርልድ ግሩፕ” ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈራ ደርበው፣ ፕላትፎርሙ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር ወደ ተሻለ ደራጃ እንደሚያሸጋግር ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ምርቶችን በተለይ ቡና በኢ-ኮሜርስ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻዎችን ለቻይና ጎበኚዎች ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡

የግራንድ ዎርልድ ግሩፕ ፕሬዚዳንት ሚ/ር ሊዮ ዋንጉያን የተደረሰውን ስምምነት በቁርጠኝነት እና በኃላፊነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በመርሀግብሩ ላይ የተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣የቡና ኩባንያዎች፣ የንግድ ማህበራት፣በቻይና የኢ-ኮሜርስ ተቋማት ተወካዮች በቀጣይ በኢትዮጵያ መሰማራት የሚፈልጉ የተለያዩ የቻይና ኩባንያ ተወካዮች መገኘታቸውን በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review