በኒውዮርክ ሲካሄድ የቆየው 69ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ጉባኤ ተጠናቀቀ

You are currently viewing በኒውዮርክ ሲካሄድ የቆየው 69ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ጉባኤ ተጠናቀቀ

AMN- መጋቢት 16/2017 ዓ.ም

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት፣ በአሜሪካ ኒውዮርክ ሲካሄድ የቆየው 69ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ጉባኤ ተጠናቅቋል፡፡

ጉባኤው በዋነኛነት የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሐግብር ፀድቆ በስራ ላይ የዋለበት 30ኛ ዓመትን በማስመልከት የድርጊት መርሐግብሩን አፈፃፀም በመገምገም ላይ ያተኮረ እንደነበርም ተመላክቷል።

ጉባኤው የቀጣይ 5 ዓመት የቤጂንግ መግለጫ አፈፃፀምን ለማፋጠን የሚረዳ የማስፈፃሚያ የድርጊት መርሐ ግብር በማፅደቅም ነው የተጠናቀቀው።

የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድንም ከተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር የጎንዮሽ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በዚህም ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጋር በሴቶችና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

በተመሳሳይ ከጌይጅ፣ ዩኤን ኤፍ ፒ ኤ እና ዪኒሴፍ ጋር በመተባበር በሴቶች እና ታዳጊ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለማስቆም የሚያስችሉ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ላይ መክሯል፡፡

እንዲሁም ከሞሮኮ ጋር የገጠር ሴቶችን በመደገፍ ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት ላይ ያተኮረ መድረክ ማካሄዱ ተገልጿል።

የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሃ ግብር በፈረንጆቹ 1995 በ11 ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እና በዋነኛነት የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ እና ሴቶችን ለማብቃት የወጣ ሰነድ ነው፡፡

መንግስታት እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት የስርዓተ ፆታ እኩልነት ለማረጋገጥ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎችንም በዝርዝር የሚያስቀምጥ ፍኖተ ካርታ ነው፡፡

ሀገራት በየ5 ዓመቱ የድርጊት መርሐግብሩን አፈፃፀም ሁሉን አሳታፊ በሆነ መንገድ የሚገመግሙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ይህንን ግምገማ በ2017 ዓ.ም በማካሄድ ሪፓርቱን አቅርባለች።

በዘንድሮው ጉባኤም የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ማህበራዊ ከለላ፣ የሴቶች መሪነትና የውሳኔ ሰጪነት ተሳትፎ፣ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት፣ የአካባቢ ጥበቃና የስርዓተ ፆታ አጀንዳዎች፣ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች እና ሌሎችም ትኩረት ተሰጥቷቸው በሰፊው ተዳሰዋል።

በትልልቅ አጀንዳዎች ላይ ለቀናት ሲመክር የቆየው ጉባኤ የቀጣይ 5 ዓመት የቤጂንግ መግለጫ አፈፃፀምን ለማፋጠን የሚረዳ የማስፈፃሚ የድርጊት መርሐግብር በማፅደቅ ተጠናቋል።

በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድንን ጨምሮ የመንግስት ተወካዮች፣ ከተለያዩ የሲቪክ ማህበራት፣ የሴቶችና ወጣቶች ድርጅቶች፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት፣ አለም አቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶች የተጣውጣጡ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review