በአማራ ክልል በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አርሶ አደሮች የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ከሽያጩ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል

AMN-ታኅሣሥ 9/2017 ዓ.ም

በአማራ ክልል በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተሳተፉ አርሶ አደሮች በምርቱ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ከሽያጩ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለጹ።

በክልሉ በዘንድሮ የበጋ ወቅት 254 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት እየተሰራ ነው።

በክልሉ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እና የሰሜን ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች እንደገለጹት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ ባህል እየተለመደ መጥቷል።

አርሶ አደር አጋሉ አምቢ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የጓንጓ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ ባለፈው ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ካመረቱት 20 ኩንታል ስንዴ ግማሹን ለገበያ በማቅረብ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ብዙም አልተለመደም ነበር የሚሉት አርሶ አደር አጋሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለስንዴ ልማት በተሰጠው ትኩረት እርሳቸውም በልማቱ በመሳተፍ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በዚህም የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ከምርት ሽያጭ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እያገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ሌላው የጓንጓ ወረዳ አርሶ አደር አልጋነህ አካል በበኩላቸው፤ በምግብ ራስን ለመቻል የጀመሩት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጨማሪ ገቢ እያስገኘላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ባከናወኑት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 10 ኩንታል አምርተው ግማሹን ለገበያ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም አንድ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት የእርሻ ዝግጅት ማድረጋቸውን እና ከዚህም የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

“በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መሳታፋችን ተጠቃሚ አድርጎናል” ያሉት ደግሞ በሰሜን ጎጃም ዞን የሰሜን ሜጫ ወረዳ አርሶ አደር አምሳሉ አለኸኝ ናቸው።

ግማሽ ሄክታር መሬት በስንዴ አልምተው ያገኙትን ከ17 ኩንታል በላይ ምርት በምግብ ራስን ለመቻል የሚያደርጉትን ጥረት ከማገዝ ባለፈ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያዘው የበጋ ወቅትም በመስኖ ስንዴ አንድ ሄክታር የሚጠጋ መሬት እያለሙ መሆኑንና ከዚህም ከ25 ኩንታል ያላነሰ ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ የአትክልት፣ መስኖና ውኃ አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ወንድምነው እንደገለጹት፤ በዘንድሮው የበጋ ወቅት 254 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት እየተሰራ ነው።

እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም ከ72 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ከ61 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን አስታውቀዋል።

በበጋው በስንዴ ከሚለመው መሬት 10 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንና በአሁኑ ወቅትም የተጠናከር የእርሻና የዘር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

ለልማቱ ውጤታማነት የባለሙያ ድጋፍ በቅርብ እየተደረገ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በክልሉ ባለፈው ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ከለማ 150 ሺህ ሄክታር መሬት ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review