በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው

AMN-ታኅሣሥ 9/2017 ዓ.ም

በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ።

በደሴ ከተማ አስተዳደር ህብረተሰቡ ከየክፍለ ከተማው በተለያየ አቅጣጫ በመውጣት ወደ ሆጤ ስታዲየም እያቀና ነው፡፡

የድጋፍ ሰልፈኞቹ መንግስት በተደጋጋሚ የሚያደርገውን የሰላም ጥሪ እንደግፋለን፣ ፅንፈኛ ሀይሎች ለህግ ይቅረቡልን፣ ክልላችንን የሰላምና የልማት ማዕከል ለማድረግ ሁላችንም ለሰላም ዘብ እንቆማለን፣ መንግስት ለሰላም መስፈን የሚወስዳቸውን እርምጃዎች እንደግፋለን የሚሉ መልዕክቶችን እያስተላለፉ ይገኛሉ።

መንግስት ህግ በማስከበር የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ሊያስጠብቅ ይገባል፣ ፅንፈኛው ሀይል በንፁሃን ላይ የሚፈፅመው ግድያ፣ ማገትና ማፈናቀል ሊቆም ይገባል፣ መከላከያ ሰራዊታችን፣ የፌዴራልና የክልላችን የፀጥታ ሀይሎች ለከፈሉት ዋጋ ክብር እንሰጣለን የሚሉም እንዲሁ።

በተመሳሳይ በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ እየተካሄደ ባለው ሕዝባዊ ሰላማዊ የድጋፍ ሰልፍ ለክልሉ ሰላም መስፈን የመከላከያ ሰራዊት የክልልና የፌዴራል የፀጥታ ሃይሎች ለከፈሉት ዋጋ ክብር እንሰጣለን፣ ሰላማችንን እናፅና ልማታችንን እናስቀጥል የሚሉና ሌሎችም መልክቶችን በማስተላለፍ ነዋሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳውኃ ከተማም እንዲሁ ህዝባዊ ሰላማዊ የድጋፍ ሰልፉ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በዚህም ሰላማዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ተሳታፊዎቹ ክልላችንን የሰላምና የልማት ማዕከል ለማድረግ ሁላችንም ለሰላም ዘብ እንቆማለን!፣ መንግስት ለሰላም መስፈን የሚወስዳቸውን እርምጃዎች እንደግፋለን! የሚሉና ሌሎች መልዕክቶች እየተስተጋቡ ነው።

በሌላ በኩልም የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችም የድጋፍ ሰልፍ እያካሄዱ ይገኛሉ።

ነዋሪዎቹ በከተማው ፋሲለደስ ስታዲየም እያካሄዱት ባለው የድጋፍ ሰልፍ ክልላችንና ከተማችን የሚያስፈልገው ጦርነት ሳይሆን ልማትና ሠላም ነው ሲሉ በያዙዋቸው መፈክሮች አስተጋብተዋል።

መንግስት ለሠላም መስፈን የሚወስዳቸውን እርምጃዎች እንደግፋለን፣ የመከላከያ ሠራዊቱና የክልሉ የጸጥታ ሀይል ለሠላም መስፈን እየከፈሉት ላለው መስዋእትነት ክብር እንሰጣለን ብለዋል እያስተጋቡት ባለው መልዕክት።

በሰልፉ ላይ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ተማሪዎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review