በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብርና እገዛ የሚበረታታ መሆኑ ተገለጸ

You are currently viewing በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብርና እገዛ የሚበረታታ መሆኑ ተገለጸ

AMN ግንቦት – 27/2017ዓም

በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብርና እገዛ ጥሩ ጅምር የታየበት መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በክልሉ ወቅታዊ የሰላምና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር)፣ በክልሉ ህግን ከማስከበር ጎን ለጎን የልማትና የሰላም ግንባታ ስራዎች በስፋት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብርና እገዛ ጥሩ ጅምር የታየበት መሆኑን አንስተው፣ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ ሊቀ መንበር ተስፋሁን አለምነህ፣ ብልጽግና ፓርቲ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ አካታችና ሁሉንም ማዕከል ያደረገ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የክልሉን ሰላም ዘላቂ ማድረግና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ዳር ማድረስ የጋራ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በኮሪደር ልማት፣ በህዳሴው ግድብ፣ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውና ሌሎች የልማት ዘርፎች የተገኙ ውጤቶችን አድንቀው፣ በሌሎች መስኮችም ስኬቶችን ለማምጣት በጋራ እንቆማለን በማለት መግለፃቸው ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በውይይት መድረኩ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የተለያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት መሳተፋቸውም ተመላክቷል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review