በአማራ ክልል የህግ የበላይነት ከማስከበሩ በተጓዳኝ አበረታች የልማት ተግባራት እየተከናወኑ ነው – የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ

You are currently viewing በአማራ ክልል የህግ የበላይነት ከማስከበሩ በተጓዳኝ አበረታች የልማት ተግባራት እየተከናወኑ ነው – የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ

AMN – የካቲት 4/2017 ዓ.ም

በአማራ ክልል የህግ የበላይነት ከማስከበሩ በተጓዳኝ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አበረታች የልማት ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ገለጹ።

የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር፤ 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን፤ 9ኛ መደበኛ ጉባኤ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

አፈ-ጉባኤዋ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፤ ችግር በመቋቋም የአመራር አባላት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ለውጥ ማምጣት ችለዋል።

ይህም በክልሉ የህግ የበላይነትን ከማስከበሩ ጎን ለጎን አበረታች የሆኑ የተለያዩ የልማት ተግባራት እንዲከናወኑ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።

እየተከናወኑ የሚገኙት የልማት ተግባራት የክልሉን ብልፅግና እና የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ እንደሆኑ ምክር ቤቱ መገንዘቡን አስታውቀዋል።

ለዚህም በየደረጃው ያሉ አመራሮች የሚወርዱ አቅጣጫዎችን በቅንጅትና በትብብር መንፈስ በመስራታቸው የመጣ ለውጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በፌዴራል መንግስስት ድጋፍ የሚካሄዱ የኮሪደር ልማት ፣ የቱሪዝም መዳረሻ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች በወቅቱ ተጠናቀው ለህዝብ ጥቅም እንዲውሉ የአመራር አባላት ክትትልና ድጋፍ አበረታች መሆኑንም አመልክተዋል።

የክልሉን ሰላም በዘላቂነት በማፅናት ህዝቡ የሚያነሳውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ተግባራቱን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።

ለዚህም የተቋማትና የሰው ሀይልን ሪፎርም በማድረግ ህብረተሰቡ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኝ መስራት ከእያንዳንዱ የአመራር አባላት የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለተከታታይ አራት ቀናት በሚካሄደው የምክር ቤቱ ጉባኤ የአስፈጻሚ አካሉና ሌሎች ተቋማት ሪፖርት ላይ ከመወያየት በተጨማሪ ሹመቶችን እንደሚያፀድቅ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review