በአቪዬሽን ዘርፍ በርካታ አደጋ የተስተናገደበት የታኀሣሥ ወር

You are currently viewing በአቪዬሽን ዘርፍ በርካታ አደጋ የተስተናገደበት የታኀሣሥ ወር

AMN – ታኀሣሥ 21/2017 ዓ.ም

እየተገባደደ ያለው የፈረንጆቹ 2024 በተለይም ታኀሣሥ ወር በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ዘንድ በርካታ አደጋዎችን በማስተናገድ እጅግ አስከፊው ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል፡፡

በዚህ ወር ከትንንሽ የግል አውሮፕላኖች ጀምሮ እስከ የንግድ ጄቶች ድረስ አደጋ አስተናግደዋል፡፡

ስድስት አውሮፕላኖች ተከስክሰው በመቶዎች የሚቆጠር የሠው ሕይወትና ንብረት የወደመበት ይህ ታኀሣሥ ወር ለአቪዬሽን ኢንዱስትሪው የጨለማ ወር ሆኗል ሲሉ መገናኛ ብዙሃን በዘገባቸው አመላክተዋል፡፡

በ29 አመቱ ወጣት ፓይለት ሮዲሪጎ አብራሪነት በአማዞን ጫካ የተከሰከሰችው “ሴሳን አውሮፕላን” የወሩ የመጀመሪያ አሳዛኝ ዜና ነበር፡፡ ከፖርቶ ቬሆስ ወደ ማኑስ በረራ ላይ የነበረችው አውሮፕላኗ ከአብራሪው በተጨማሪ አንድ ተሳፋሪ አሳፍራ ነበር፡፡

አውሮፕላኑ ከራዳር እይታ ውጭ በመሆኑ ፍለጋውን አስቸጋሪ አድርጎት የነበረ ቢሆንም ከአደጋው አራት ቀናት በኋላ ስብርባሪውን ማግኘት ተችሏል፡፡

በፈረንጆቹ ታኀሣሥ 25 ቀን 2024 ላይ የአዘርባጃኑ አውሮፕላን በአወዛጋቢ ሁኔታ ተከስክሶ ከ79 መንገደኞች መካከል የ38 ሰዎችን ህይወት በመቅጠፍ ለአቪዬሽኑ ሌላ አስደንገጭ ዜና ይዞ ብቅ አለ፡፡

የበረራ ቁጥር 8243 የሆነው ኤምብረር 190AR የተሰኘው ንብረትነቱ የአዘርባጃን የሆነው አውሮፕላን ከባኩ ወደ ሩሲያዋ ግሮንዚ በሚያደርገው በረራ ወቅት በሚሳኤል ተመትቶ መውደቁ ተነግሯል፡፡

ሚሳኤሉ ከሩሲያ የተተኮሰ ነው ቢባልም ፕሬዝዳንት ፑቲን ለአደጋው ኃላፊነት አለመውሰዳቸውን በሚያሳይ መልኩ ይቅርታ መጠየቃቸውም ይታወሳል፡፡አሁንም ድረስ የአደጋውን መንስዔ ማጣራቱ እንደቀጠለ ነው፡፡

በአውስትራሊያም አነስተኛ አውሮፕላን ተከስክሳ ሲያበራት የነበረው የአውሮፕላኗ ባለቤት የሆነው የ67 ዓመት ግለሰብ ወዲያው ህይወቱ አልፏል፡፡ አብሮት የነበረው የ32 ዓመት ልጁ ደግሞ ለከፍተኛ ጉዳት ተዳርጓል፡፡

በደረሰው አደጋ በአስገራሚ ሁኔታ የ182 ሰዎች ነፍስም ከአደጋ የተረፈው በዚሁ ወር ነበር፡፡ ንብረትነቱ የኔዘርላንድ የሆነው ኬ.ኤል.ኤም ፍላይት 1204 ከኖርዌይ ወደ አመስተርዳም 182 መንገደኞችን አሳፍሮ ከመነሻው ችግር አጋጥሞት ለማረፍ ሲሞክር አደጋ ደርሶበታል፡፡ ነገር ግን በውስጡ የነበሩ የ182 ሰዎች ሕይወት መትረፍ ችሏል፡፡

በትናንትናው ዕለት በደቡብ ኮሪያ እጅግ አሳዛኝ የሚባል የአውሮፕላን አደጋ ተከስቷል፡፡ ጄጁ አውሮፕላን በረራ ቁጥር 2216 የሆነው ቦይንግ 737 ተከስክሶ የ176 ሰዎችን ህይወት ለህልፈት ዳርጓል፡፡ የአደጋው መንስኤውም በምርመራ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡

በደቡብ ኮሪያ ከደረሰው አደጋ አንድ ሰዓት በኋላ ደግሞ ኤር ካናዳ 2259 ሌላ አደጋ አስተናግዷል፡፡ በእርግጥ መንገደኞችን በሠላም ከአውሮፕኗ ማውጣት ተችሏል፡፡

እየደረሱ ያሉ የአውሮፕላን አደጋዎች በዓለማችን የተሻለ የተባለለትን የአየር ትራንስፖርት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ እየሆነ መጥቷል፡፡ የአቪዬሽን ባለሥልጣናትም የደህንነት መለኪያቸውን ዳግም እንዲያጤኑት እድል የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡

በታኀሣሥ ወር የተከሰቱ የአውሮፕላን አደጋዎች ለአቪዬሽኑ ዘርፍ ታኀሣሥን የጨለማ ወር ያስባለ እና ዓለም ሀዘን ውስጥ የወደቀችበት ወር መሆኑንም መገናኛ ብዙሃኑ በዘገባቸው ዳሰዋል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review