AMN – የካቲት 6/2017 ዓ.ም
በብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዐት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና ኃላፊ በአቶ አደም ፋራህ የተመራው የኢፌዲሪ መንግስት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በአለም መንግስታት ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛል።
3ኛ ቀኑን በያዘው በተባበሩት አረብ ኤመሬቶች ዱባይ እየተካሄደ የሚገኘው የአለም መንግስታት ጉባዔ ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ያላትን መንግስታዊ የአስተዳደር ልምዶች በአቶ አደም ፋራህ አማካኝነት ለጉባዔው አቅርባለች።
በቀረበው ገለፃም ባለፉት 6 ዓመታት በብልፅግና ፓርቲ በሚመራው መንግስት በተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች በኢኮኖሚ፣በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ መስኮች ተጨባጭ ድሎችን ማስመዝገብ መቻሉን አቶ አደም ገልፀዋል።
በተለይም በድህነት ቅነሳ፣በሰው ተኮር ተግባራት፣አዳዲስ ኢኮኖሚያዊ እመርታዎችን በመፍጠር፣በምግብ ራስን ለመቻል በተደረጉ ጥረቶች እንዲሁም ያልታዩ ሀገራዊ ፀጋዎችን ለይቶ በመጠቀም ረገድ የተገኙ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ስልታዊ አይበገሬነትን ለማረጋገጥም ቴክኖሎጂን መሰረት በማድረግ ተግባራዊ በተደረጉ እርምጃዎች አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን፣ለውስብስብ ችግሮች ቀላል መፍትሄዎችን ማፍለቅ መቻሉንና ይህ ሀገራዊ ውጥን ግቡን እንዲመታ የተባበሩት አረብ ኤመሬቶችን የመሰሉ ሀገራት 5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮችን በማሰልጠን ድጋፍ እያደረጉ በመሆናቸው እንደ ሀገር ያለን አክብሮት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በተግዳሮት የማይናወጥ ቋሚ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ማህበራዊ ዋስትና እና ጠንካራ መንግስታዊ አስተዳደርን መገንባት ስልታዊ አይበገሬነትን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት በማመን ሀገር በቀል በሆነው የመደመር እሳቤ ተመርታ ወደ ብልፅግና የምታደርገው ጉዞ ውጤታማ መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይም እንደ ሀገር የተመዘገቡ ስኬቶችን በተሰናሰለ መልኩ ለማስቀጠል ሀገራችን ኢትዮጵያ መርህን ባከበረ መልኩ ከሀገራት ጋር ለጋራ ተጠቃሚነት በጋራ ለመስራት ሁሌም ቢሆን በሯ ክፍት እንደሆነ ማብራራታቸውን የፓርቲው መረጃ ያመለክታል።




All reactions:
4141