AMN – ታኅሣሥ 11/2017 ዓ.ም
የአንካራው ስምምንት ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ስታቀርበው ለነበረው እና አብዛኛውን ጊዜ ትኩረት ሳያገኝ ለቆየው የባህር በር ጥያቄዋ ምላሽ የሰጠ፣ በሀገሪቱ ዲፕሎማሲያዊ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑ እየተገለጸ ይገኛል።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ጥናት ዳይሬክተር ጄኔራል ግዛቸው አስራት (ዶ/ር) በዚሁ ጉዳይ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ “በሶማሊያ እና በቱርኪዬ እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሀገራት እውቅና የተሰጠው ይህ ስምምነት፣ የኢትዮጵያን የባህር በር መሻት ሕጋዊነት ያረጋገጠ፣ ጉዳዩን በዓለም አቀፍም ሆነ ቀጣና አቀፍ መድረኮች ላይ ማንሣት እንደነውር ይቆጠር የነበረውን አስተሳሰብ የሰበረ ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው የአፍሪካ ቀንድ የለውጥ እርምጃ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ላለፉት 30 ዓመታት ሊደረስበት የማይችል ነው የተባለውን ግብ በማደስ ረገድ ሥልታዊ እመርታ ነው ይላሉ።
የኢትዮጵያ የባህር መዳረሻን መሻት ከአሁን ወዲህ ወደ ፖሊሲ ክርክሮች የሚወርድ ጉዳይ ሳይሆን እንደ ሀገር እና ቀጣናዊ ጠቀሜታ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ነው ያነሡት።
ይህ ለውጥ ኢትዮጵያ የንግድ ኮሪዶሯን ማብዛት እና የሎጂስቲክስ ማዕቀፏን ማዘመን ያለባትን አንገብጋቢ ፍላጎት ያሳያል ያሉት ዶክተር ግዛቸው፣ የባህር ተደራሽነት ሀገሪቱ በተለመደው ወደብ አልባ የንግድ መስመሮች ላይ ከመተማመን ይልቅ ወጪ ቆጣቢነትን በማረጋገጥ ቀጣናዊ የንግድ ትሥሥርን በማጠናከር እንድትጓዝ እንደሚያስችላት አብራርተዋል።
በተጨማሪም፣ ከባህር ተደራሽነት ጋር ተያይዘው የሚገኙ እንደ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ያሉ የኢኮኖሚ ዕድሎችም በቀላሉ የሚታዩ እንዳልሆኑ ጠቅሰዋል።
የስምምነቱ ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜታ ደግሞ ኢትዮጵያ ለሰላማዊ ድርድር እና ችግሮችን በትብብር ለመፍታት ያላትን ቁርጠኝነት ማረጋገጡ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
ይህ አካሄድ የኢትዮጵያ መንግሥት የባህር በር ተደራሽነትን ለማግኘት በፀብ ሳይሆን በውይይት እና በጋራ መግባባት እንዲሆን ያለውን ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቅ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትክክል እንደገለጹትም የባህር በር መዳረሻ ጉዳይ የሀገር ኅልውና ጉዳይ መሆኑን ያረጋገጡት ዶክተር ግዛቸው፣ የአንካራው ስምምነት ዲፕሎማሲያዊ ድል ከመሆኑም ባሻገር ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ መረጋጋት እና ውህደት ያላትን ቁርጠኝነት በጉልህ የሚያፀባርቅ እንደሆነ በጽሑፋቸው አትተዋል።
ስምምነቱ ለሶማሊያም ኢኮኖሚያዊ እና የደኅንነት ትሩፋቶችን መያዙን በደንብ መገንዘብ እንደሚገባ አስታውሰው፣ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሉዓላዊነት እውቅና በመስጠት እና በማክበር የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው የበለጠ የሚጠናከርበትን ሁኔታ እንዳመቻቸች ጠቁመዋል።
የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን በማፅናት ረገድ ያላትን ሚና አጉልቶ ያሳየ ነው የሚሉት በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ጥናት ዳይሬክተር ጄኔራል ግዛቸው አስራት (ዶ/ር)፣ ይህም ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሰላም ማስከበርን እና ሽብርተኝነትን መከላከልን ጨምሮ ለሀገሪቱ ለከፈለችው ከፍተኛ መሥዋዕትነት እውቅና የሰጠ እንደሆነ አብራርተዋል።
ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል መተማመን እንዲፈጠር በማድረግ እና ለረጅም ጊዜ ቀጠናዊ ትብብርን ሲያዳክም የነበረውን ውጥረት በማርገብ ለሰላም የራሱ አበርክቶ እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል።
ከዓለም አቀፋዊ ዕይታ አንፃርም የስምምነቱ ለዓላማዎች ሰፊ ድጋፍ እንደተሰጣቸው ጠቁመው በተለይ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ለስምምነቱ የሰጡት ድጋፍ የስምምነቱን ተዓማኒነት የሚያጠናክር ብቻ ሳይሆን በቀጣናው ካለው ዓለም አቀፍ ፍላጎቶች ጋር የሚጣጣም እንደሚያደርገው አንሥተዋል።
ኤርትራ እና ግብጽን የመሳሰሉ ጎረቤት ሀገራት በጉዳዩ ላይ ሐሳብ ከመስጠት መቆጠብን ቢመርጡም ስምምነቱ በቀጣናው መቀራረብ እና ትብብር እንዲኖር ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ነው በጽሑፋቸው የጠቆሙት።
ኢትዮጵያ ለአንካራው ስምምነት የሰጠችው ትኩረት ሀገሪቱ መተማመንን መገንባት እና የጋራ ጥቅሞችን የመለየት አስፈላጊነት ላይ ያላትን ቁርጠኛ አቋም የሚያንፀባርቅ እንደሆነም አመልክተዋል።
ከእነዚህ መሠረታዊ ነገሮች ውጪ ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ ያለመተማመን እና አለመረጋጋት አዙሪት ውስጥ የመቆየት አደጋ እንደሚጋረጥበት ነው ያሳሰቡት።
ለዘላቂ ሰላም ለማምጣት እና ለኢኮኖሚያዊ ብልፅግና መሠረት ለመጣል የቀጣናው መንግሥታት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይህንን ዕድል ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ምክር ለግሰዋል።