በአዋሽ መልካሣ ወረዳ በተካሄደ የተቀናጀ የህግ ማስከበር ዘመቻ 38 የአሸባሪው ሸኔ ቡድን አባላት እጅ ሰጡ

AMN- ህዳር 4/2017 ዓ.ም

በአዋሽ መልካሣ ወረዳ በተካሄደ የተቀናጀ የህግ ማስከበር ዘመቻ 38 የአሸባሪው ሸኔ ቡድን አባላት እጅ መስጠታቸውን የአዳማ ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ አስታወቀ።

ከ38ቱ መካከል ስድስት የአሸባሪው ሸኔ ቡድን አባላት የሰላም መንገድን በመምረጥ ከነሙሉ ትጥቃቸው ዛሬ ለአዳማ ከተማ ፖሊስ እጅ መስጠታቸውን መምሪያው ገልጿል።

እጅ የሰጡ የሽብር ቡድኑ አባላትም በአዋሽ መልካሣ ወረዳ የጥፋት ድርጊት ሲፈጽሙ የቆዩ መሆናቸውንም ነው የከተማው ፖሊስ ያስታወቀው።

የአዳማ ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ የወንጀል መከላከል ዘርፍ አዛዥ ኮማንደር አብደላ ቡተና እንደገለፁት ባለፈው አንድ ወር የተቀናጀ የህግ ማስከበር ዘመቻ ሲካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የአካባቢው የፀጥታ ሀይሎች ተቀናጅተው ባካሄዱት ዘመቻ አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥ ማስቻሉን አንስተዋል።

በተከናወነው የህግ ማስከበር ዘመቻ ዛሬ እጃቸውን የሰጡትን ጨምሮ 38 የሸኔ ሽብር ቡድን አባላት በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለፀጥታ ሀይል መስጠታቸውን ነው የተናገሩት።

አሁንም የጸጥታ ሀይሉ የሰላም አመራጭ ተከትለው የሚመጡ የአሸባሪው ቡድን አባላትን እንደሚቀበል ገልጸዋል።

አሁንም ከመከላከያና ፌዴራል ፖሊስ እንዲሁም ከአርሲ እና ከምስራቅ ሸዋ ዞኖች ጸጥታ ሀይሎች እና የአካባቢው ሚሊሻ ጋር በመቀናጀት የህግ ማስከበሩ ስራ መቀጠሉን አስታውቀዋል።

እጃቸውን ከሰጡ የአሸባሪው ቡድን አባላት መካከል በአዋሽ መልካሳ አካባቢ የሚንቀሳቀሰው ቡድን መሪ መሆኑ የተገለጸው ታሪኩ ዳዲ አንዱ ሲሆን፤ ቡድኑ ለህዝብ እታገላለሁ እያለ ህብረተሰቡን የማሰቃየት ተግባር ስፈፅም ነበር ብሏል።

ቡድኑ ለህዝብ በእውነት የሚታገል መስሎን ነበር ከቤት የወጣነው፤ አሁን መገዳደል ይቅር ብለን የሰላም መንገድ መርጠን እጅ ሰጥተናል ሲልም ተናግሯል።

አሁንም በየጫካው የሚገኙ የቡድኑ አባላት ከመገዳደልና መጠፋፋት ትርፍ እንደማይገኝ ተገንዝበው በሰላም እንዲመለሱ መልዕክቱን አስተላልፏል።

የአዳማ ከተማ የአዋሽ መልካሳ እና ወንጂ ከተሞችን ጨምሮ ከምስራቅ ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች 28 የገጠር ቀበሌዎችን በማካተት ዳግም መዋቀሯ የሚታወስ ሲሆን የአዋሽ መልካሳ ወረዳም በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚተዳደር መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review