AMN- የካቲት 26/2017 ዓ.ም
በአዉሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ ከሜዳዉ ዉጭ ሰባት ግቦችን ሲያዘንቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ነዉ። ከየትኛዉ ቦታ ግብ ማስቆጠር የሚችሉ ተጨዋቾች እንዳሉት በሚገባ ያሳዩበት ምሽት ሁኖም አልፏል፡፡
መድፈኞቹ በአዉሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ ትናንት ምሽት ከሜዳቸዉ ዉጭ ፒ ኤሲ ቪ ኢንድሆቨንን 7ለ1 በሆነ ዉጤት በማሸነፍ አዲስ ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡
ከጨዋታዉ በፊት በእንደዚህ ሰፊ የግብ ልዩነት ጨዋታዉ ይጠናቀቃል ብሎ የገመታ ባይኖርም የሚካኤል አርቴታዉ ስብስብ አርሰናል ይህንን ለአለም የስፖርት ቤተሰብ አሳይቷል፡፡
የጨዋታዉ ከከብ ማርቲን ኦዲጋርድ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ፤ጁሊያን ቲምበር፤ኢታን ንዋኔሪ፤ሚካኤል ሜሪኖ፤ሊአንድሮ ትሮሳርድ እና ሪካርዶ ካላፊኦሪ ግቦቹን አስቆጥረዋል፡፡

ጨዋታዉን በቢቢሲ ራዲዮ 5 በቀጥታ ሲተነትን የነበረዉ የቀድሞዉ እንግሊዛዊ ኢንተርናሽናል ክሪስ ሱተን ከጅምሩ አርሰናል ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ነበር ይህ ለቀሪው የውድድር ዘመን ትልቅ መተማመንን ይሰጣቸዋል ሲል ተናግሯል፡፡
ማርቲን ኦዲጋርድ ወደ ጥሩ ብቃቱ እየተመለሰ ነዉ የመሃል ተከላካዮቹ ገብርኤ ማጋሌስ አና ዊሊያም ሳሊባ ምርጥ ጥምረትም ነበር አረሰናል በምሽቱ ጨዋታ በአጨራረስ ጨካኝ ነበር ሲልም አክሏል፡፡
ከጨዋታዉ መጠናቀቅ ቡሃላ የመድፈኞቹ አሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታም በቡድኑ እንቅስቃሴ በጣም እንደተደሰተ ተናግሯል ፤፤
በመናበብ እና ጥሩ ጥምረት በማሳየት አዝናኝ ጨዋታ አድርገን አሸንፈን ወጥተናል ሲል ተናግሯል።

ከአርሰናል አካዳሚ የተገኘዉ የ17 አመቱ ታዳጊ ኢታን ንዋኔሪ ያሳየዉን ምርጥ ብቃትም አምሽቷል።
ኢታን ንዋኔሪ በቀኝ መስመር የማጥቃት ሚናዉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱም ሁነኛ የቡካዮ ሳካ ቦታን የሸፈነ ጀግና እንዲባልም አድርጎታ። በዉድድር አመቱ በሁሉም ባደረጋቸዉ 28 ጨዋታዎች 8 ግቦችንም ከመረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል፡፡
አርሰናል በሩብ ፍጻሜዉ ከሪያል ማድሪድ እና ከአትሌቲኮ ማድሪድ አሸናፊ ጋር መገናኜቱም ከወዲሁ ተጠባቂ አድርጎታል፡፡
በአለማየሁ ሙሳ