በታክሲ ተርሚናሎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስተካከል እና ነባር ተራ አስከባሪዎችን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር እንዲሁም ለከተማዋ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ደንብ አፅድቆ ወደስራ መግባቱ ይታወሳል።
በደንቡ መሰረትም የከተማዋ የስራና ክህሎት ቢሮ፣ ነባር ተራ አስከባሪዎች ወደ ተለያዩ የስራ መስኮች የሚሸጋገሩበትን ሁኔታ በማመቻቸት አዲስ የተርሚናል ኢንተርፕራይዞችን አደራጅቶ ስራ አስጀምሯል።
ዛሬ ስራ የጀመሩት ወጣቶች ቁጥር 996 ሲሆን ከአሁን በፊት የስራ እድል ያልተፈጠረላቸው መሆኑ በስራና ክህሎት ቢሮ በኩል ተለይቶ በ87 ኢንተርፕራይዞች እንዲደራጁ መደረጉ ተነግሯል።
ወጣቶቹ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ተራ የማስከበር፣ የተርሚናሎችን ደህንነት የመጠበቅና የመቆጣጠር ስራ ያከናውናሉም ተብሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ እና ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ወጣቶችን ለማደራጀት በቅንጅት መስራታቸው ተመላክቷል።
ነባር ተራ አስከባሪዎች በመረጡት የሙያ መስክ እንዲሰማሩ ቢሮው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ በምክትል ከንቲባ ማእረግ የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ተናግረዋል።
በካሳሁን አንዱዓለም