AMN – የካቲት 21/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተመራ ያለው የፋይዳ ምዝገባ አፈፃፀም ተገምግሞ የተማሪዎች ምዝገባ ይፋ ሆኗል፡፡
የሃገር አቀፉ የፋይዳ ምዝገባ ስርዓት ለሃገር የሚኖረውን አስተዋፅዖ ከግምት በማስገባት የስርዓቱን ተፈፃሚነት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለማስተባበር የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ከሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ በጋራ እየመሩት ያለ ሲሆን ከከተማ አስተዳደሩ ተቋማት አገልግሎት ጋር በተያያዘም አስገዳጅ አሰራር ተዘርግቷል።
ይህንኑ መነሻ በማድረግ በዛሬው ዕለት እየተደረገ ያለው ምዝገባ ዝርዝር አፈፃፀም ገለፃ ቀርቦ ግምገማ ተደርጓል።
ላለፉት ወራት በተፈጠረው የጋራ ንቅናቄ በከተማው ከ2.1 ሚልዮን በላይ አዲስ ተመዝጋቢ መመዝገብ የተቻለ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን 900ሺ የሚጠጋው ምዝገባ በቀጥታ በሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ መዋቅር ጽ/ቤቶች የተደረገ ምዝገባ መሆኑ በሪፖርት ቀርቧል።

በዛሬው ዕለት በይፋ የተጀመረው የትምህርት ቤት ተማሪዎች ምዝገባ ንቅናቄ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን የሚመራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በላይ የሆናቸው ህፃናት በዘመቻ ምዘገባ እንደሚከናወን ተነግሯል። ለዚህም የትምህርት ማህበረሰቡን እና የተማሪ ወላጆችን ከሚወክሉ አደረጃጀቶች ጋር ውይይት በዝግጅት ምዕራፍ ተከናውኗል።
የፋይዳ ምዝገባ ቁጥር በአዲስ አበባ የመንግስት ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት በቅድመ ሁኔታነት የተቀመጠ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በከተማው ያሉ የመንግስት ሰራተኞች የቅጥር እና ዝውውር እንዲሁም የደመወዝ አከፋፈል ስርዓት ከምዝገባ ስርዓቱ ጋር እንዲቀናጅ በአስገዳጅ ስርዓትነት መቀመጡን የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ መረጃ ያመላክታል፡፡
የከተማው ትምህርት ቢሮ የልደት እና የፋይዳ ምዝገባ የ2018 ዓ.ም የተማሪዎች የትምህርት ቤት ምዝገባ ቅድመ ሁኔታም እንደሆነ ይፋ አድርጓል።
በመድረኩ ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ዋና ስራ-አስሊያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ፣ የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ አለማየሁ እጅጉ ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ዮዳሄ አርዓያስላሴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ እንዲሁም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ተገኝተዋል፡፡