በአዲስ አበባ ከተማ የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር የተከናወኑ ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ማስገኘታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በበኩላቸው ከተማዋ የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር እያከናወነች ያለችው ስራ ለቀሩት የሀገሪቱ አካባዎች ትልቅ ተሞክሮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የላፍቶ ቁጥር ሁለት ሁለገብ የገበያ ማዕከልን ምርቀው ለአገልሎት ክፍት አድርገዋል፡፡
በዚህ መርሃ ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በከተማዋ የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር ተጨባጭ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዚህ ስራ ዋና ማሳያው ባለፉት ዓመታት ደራጃቸውን የጠበቁ የገበያ መዕከላት በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች መገንባታቸው መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች እነዚህ የገበያ ማዕከላት የኑሮ ውድነትን እና የገበያ ሁኔታን ከማስተካከል አንጻር ያስገኙት ውጤት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የገበያ መዛባት እና የኑሮ ውድነቱን መሰረት በማድረግ የላፍቶ ቁጥር ሁለት ሁለገብ የገበያ ማዕከል መገንባቱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል፡፡
የገበያ ማዕከሉ በ8.8 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች ከመጀመሪያው የገበያ ማዕከል ጋር ሲደመር ከ13 ሄክታር በላይ መሬት እንደሚሸፍን ተናግረዋል፡፡
በዘርፉ የተጀመሩ ስራዎችን የበለጠ በማጠናከር ለህዝብ የተገቡ ቃሎች በተግባር የመፈጸም ስራ እንደሚቀጥልም ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል፡፡
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) መንግስት የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን በመጠቆም ከነዚህ መካከል በቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች ላይ የተከናወኑ ስራዎች የሚጠቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በመላው ሀገሪቱ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎችን ቁጥር 1493 ማድረስ መቻሉን ገልጸው በዚህ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ ስራዎች የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱ እና ትልቅ ተሞክሮ የሚቀሰምባቸው መሆኑን ተናረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ተሞክሮ በከተማዋ ብቻ የሚቀር ሳይሆን በመላው ሀገሪቱ እየተስፋፋ ያለ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ የኑሮ ውድነትን ለመከላከል እና የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አድናቆት የሚቸራቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሃብታሙ ሙለታ