AMN – ጥር 6/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ከከተማዋ የደብር አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች ጋር ውይይት እያደረገ ይገኛል።
በዓሉ ሃይማኖታዊ እሴትና ስርዓቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር የበዓሉ ባለቤት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዝግጅት ማጠናቀቋን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ተናግረዋል።

ብሔራዊ በዓል የሆነው የጥምቀት በዓል መንፈሳዊ ፣ ባህላዊ እንዲሁም ማህበራዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ደግሞ የጉባኤው ዋና ጸሐፊ መጋቤ ታምራት አበጋዝ ተናግረዋል።
በሁሉም የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች በዓሉ ያለምንም ችግር በድምቀት እንዲከበር አስፈላጊ የፀጥታ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ተናግረዋል።

ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው ከፍ ያለ ቁጥር ባለው ምዕመን ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባህር ሲያመሩና ሲመለሱ እያንዳንዱ ክንውን አስተማሪና ሃይማኖታዊ ስርዓቱን የጠበቀ መሆን እንዳለበት የሃይማኖት አባቶች አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ ከ255 አብያተ ክርስቲያናት የሚወጡ ታቦታት ወደ 65 የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች የሚሄዱ ሲሆን ከ4 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ፣ ከ30 ሺህ በላይ ካህናት እና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የሰንበት ተማሪዎች በበዓሉ ላይ እንደሚታደሙ የአዲስ አበባ ሀገር ስብከት መረጃ ያመላክታል።
በካሳሁን አንዱዓለም