በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን አቅም የማሳደግ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

You are currently viewing በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን አቅም የማሳደግ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

AMN- ጥር 20/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን አቅም የማሳደግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየተከናወነ የሚገኘውን የአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያና ማሰራጫዎችን መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት በያዝነው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑንም አገልግሎቱ አስታውቋል።

በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በ50 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ውስጥ የስርጭት መስመሮችን አቅም በማሳደግ ተጨማሪ የኃይል ፍላጎቶችን እንዲያስተናግድና የኃይል ብክነትን ለመቀነስ እንዲሁም መሰረተ ልማቱን ከአንድ ማዕከል ሆኖ ለመቆጣጠር የሚያስችለው ፕሮጀክት 87 ነጥብ 94 በመቶ ሥራው መጠናቀቁ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ ረጅም ጊዜ ያገለገሉ የእንጨት ምሰሶዎችን በኮንክሪት መቀየርን ጨምሮ መስመሮቹን በተሻለ ጥራት በማደስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኃይል ፍላጎት እንደሚያረካ እና ከመስመሮች እርጅና ጋር ተያይዞ የሚፈጠርን የኃይል መቆራረጥ በእጅጉ እንደሚቀንስ ይታመናል ብሏል፡፡

እስከ አሁንም 9 ሺህ 644 የእንጨት ምሰሶዎች በኮንክሪት ምሰሶ ተቀይረው፤ 347 ነጥብ 39 ኪሎ ሜትር በቀላል ንክኪ ምክንያት ኃይል እንዳይቋረጥ የሚያደርጉ ሽፍን የመካከለኛ መስመር ዝርጋታም ተከናውኗል።

በተለያዩ ምክንያቶች የኃይል መቆራረጥ ቢፈጠር እንኳ መሥመሩን ከአንድ ቦታ ሆኖ ለመቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂን ያካተተ በመሆኑ፤ ችግሩ የተፈጠረበትን ትክክለኛ ቦታ ያመላክታል ሲልም አገልግሎቱ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ይህ ቴክኖሎጂ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ በ50 ኪሎ ሜትር ዙሪያ የሚገኙ 41 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችንና 226 መለስተኛ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችን የሚያገናኝ ቴክኖሎጂ መሆኑን የገለጸው አገልግሎቱ ሥራው 65 በመቶ መጠናቀቁን አመላክቷል።

አራት አዳዲስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተገንብተዋል፤ ለአምስት ነባር የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የአቅም ማሳደግ ሥራም ተሰርቶላቸው አገልግሎት እየሰጡ ነው ሲልም ገልጿል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review