AMN – የካቲት 30/2017 ዓ.ም
“ዓላማ ተኮር፣ የተናበበ እና የተቀናጀ የተግባቦት ሥርዓት ለእመርታዊ ዕድገት” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ያለው የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የጋራ ጉባኤ ተሳታፊዎች የአዳማ ከተማን “ስማርት አዳማ ፕሮጀክትን” ጎብኝተዋል።
የከተማዋ የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ የመንግሥትን አሠራር ሥርዓት ከማዘመኑም በላይ ለማኅበረሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ያስቻለ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር ) ገልጸዋል።
ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሠሩ ያሉ አካታች እና ሁሉን አቀፍ የዲጂታላይዜሽን፣ የልማት ኢኒሼቲቮች እያመጡ ያሉትን ለውጥ ለኅብረተሰቡ ከማስገንዘብ እና ከማሳተፍ አንጻር የኮሚኒኬተሩ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑንም ዶ/ር ለገሰ አስገንዝበዋል።
የስማርት አዳማ ፕሮጀክት የከተማዋን የፀጥታ እና የመልካም አስተዳደር ችግር በእጅጉ ያሻሻለ እንደሆነ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በከተማዋ በልዩ ትኩረት እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትም ተጎብኝተዋል። የተቀናጀ የወተት ላሞች፣ የዓሣ፣ የዶሮ ዕርባታ እና የአትክልት እና ፍራፍሬ የልማት ሥራዎችን የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች ጎብኝተዋል።

የጉብኝቱ ተሳታፊዎች እየተተገበሩ ያሉ የቴክኖሎጂ እና የልማት ሥራዎችን ከማስተዋወቅ ባለፈ ለየክልላቸው የቴክኖሎጂ ሽግግር ልምድ የቀሰሙበት፣ የጋራ መስተጋብራቸውን ያጠናከሩበት እንደነበር ገልጸዋል።
በአዳማ የተጀመረው የስማርት አዳማ ፕሮጀክት የሚደነቅ መሆኑንን በማመላከት በቀጣይም ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችም ማስፋት እንደሚገባና ለዚህም በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ለማገዝ ልምድ እንዳገኙ ተናግረዋል።
እንደ ሀገር ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሠሩ ባሉ አካታች እና ሁሉን አቀፍ የከተማ መሠረተ ልማት እና የከተማ ግብርና ውጥኖች እየመጡ ያሉ ለውጦችን ለኅብረተሰቡ ከማገስዘብ እና ከማሳተፍ አንጻር የኮሙኒኬተሩ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑም መገለጹን ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።