በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ሀሳባችንን በነፃነት እያቀረብን ነው – በአማራ ክልል የህብረተሰብ ወኪሎች

You are currently viewing በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ሀሳባችንን በነፃነት እያቀረብን ነው – በአማራ ክልል የህብረተሰብ ወኪሎች

AMN – መጋቢት 29/2017

በባህር ዳር እየተካሄደ ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ሀሳባቸውን በነጻነት በማቅረብ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን በአማራ ክልል የህብረተሰብ ወኪሎች ገለጹ።

የህብረተሰብ ወኪሎቹ አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ሂደት ዛሬም በባህርዳር እንደቀጠለ ይገኛል።

በአጀንዳ ማሰባሰቡ ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙት ወኪሎች መካከል አቶ ግርማ ወልደሃና እንደገለጹት፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችንና አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት ይገባል።

ቀደም ሲል በነበሩ ችግሮች ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳቶች እንደደረሱ አስታውሰው፣ አሁን ላይ በክልልም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት እየተከናወነ ያለው ተግባር ዘመኑን የሚመጥንና ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ያለ ምክክር መፍትሄ እንደሌለ አንስተው፣ አሁን የተጀመረው አሳታፊ አጀንዳ የማሰባሰብ እንቅስቃሴም ፍቱን መፍትሄ ያመጣል የሚል ፅኑ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

እየተሳተፉበት ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትም ፍፁም ነፃ በሆነ መንገድ ያለምንም የሃሳብ ገደብ እየተሳተፉ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሌላው ተሳታፊ ሰይድ መሃመድ በበኩላቸው፣ ችግሮችን በመነጋገርና በመመካከር መፍታት ባህል መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

ችግሮችን በምክክር ለመፍታት እየተሄደበት ያለው ርቀት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በዚህ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ የህዝብ ጥያቄዎች በነፃነት እየቀረቡ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ይህም ዘላቂ መፍትሄ የሚያስገኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ማለት እኛ ዜጎቿ ነን፤ ከዚህም የመጣነው ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ለመምከር ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ ተሳታፊ ሃብታም አራጋው ናቸው።

በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ በተሞላበት መንገድ የህዝብ ጥያቄዎች ያለ ገደብ እያቀረብን እንገኛለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሃሙድ ድሪር፤ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ በየደረጃው እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያግዝ መሆኑን አስታውሰዋል።

ቀደም ሲል በሌሎች ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ መከናወኑን አስታውሰው፣ የአማራ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትም በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል ተገኝተን ከህዝባችን ጋር በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለኢትዮጵያ ይበጃል የተባሉ ሃሳቦች ሁሉ እየቀረቡ ነው ሲሉም ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እስከ ሚያዚያ 4/2017 ዓ.ም እንደሚቆይ ተመልክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review