በአፋር ክልል ዶፋን ተራራ ላይ የተከሰተው እሳተ ገሞራ ሳይሆን የእንፋሎት ውኃ በኃይል እየተወረወረ በመውጣቱ የተፈጠረ ክስተት ነው – አታላይ አየለ (ፕ/ር)

AMN – ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም

ዛሬ በአፋር ክልል ዱለቻ ወረዳ ዶፋን ተራራ ላይ የተከሰተው ጭስ እና እንፋሎት የሚመስል ነገር እሳተ ገሞራ ሳይሆን በሙቀት አካባቢ ያለው የእንፋሎት ውኃ በኃይል እየተወረወረ በመውጣቱ የተፈጠረ ክስተት መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ ሕዋ ሣይንስ እና አስትሮኖሚ ተቋም የሴስሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ሣይንስ መምህር እና ተመራማሪ አታላይ አየለ (ፕ/ር) ተናገሩ።

ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት ተመራማሪው በተፈጠረው ሁኔታ እሳት እንደማይታይ እና ወደፊት አለት ሊረጭ እንደሚችል አመላካች ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ከመስከረም ወር ጀምሮ በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ንዝረቱ እየተሰማ መሆኑንም አስታውሰዋል።

ከሰሞኑም በሬክተር ስኬል ከፍ ያሉ የመሬት መንቀጥቀጦች በፈንታሌ እና ዶፈን አካባቢ መከሰታቸውን ገልጸዋል።

የመሬት መንቀጠቀጡ በተደጋጋሚ መከሰቱ በአካባቢው እንዲሁም ንዝረቱ በሚሰማባቸው አካባቢዎች ጫና እየፈጠረ መሆኑን ያወሱት ተመራማሪው፣ በተለይም በአካባቢው በነበሩ በባህላዊ መንገድ የተሠሩ ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

የዚህ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች እየተሰማ መሆኑን እና ለዚህም መደረግ አለበት ስላሉት የጥንቃቄ እርምጃ ተመራማሪው አብራርተዋል።

ቁምሳጥን ላይ የሚቀመጡ ውድ እና ተሰባሪ እንዲሁም ተቀጣጣይ የሆኑ ዕቃዎችን መሬት ላይ ማስቀመጥ፣ ቅጽበቱ እስኪያልፍ ማዕዘን አካባቢ መቆም፣ ጠረጴዛ ስር እና ጭንቅላትን መከላከል በሚያስችል ቦታ መከለል መደረግ ካለባቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች መካከል መሆናቸውን ነው የገለጹት።

እነዚህ በየትኛውም ሀገር የሚተገበሩ ምክረ-ሐሳቦች መሆናቸውን እና መተግበር አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።

የመሬት መንቀጥቀጥን መተንበይ አይቻልም ያሉት ዶክተር አታላይ፣ ያደጉ ሀገራት የጥፋት መጠኑን ሕዝባቸውን በማስተማር እንዲሁም በሕንፃ አሠራር ቴክኖሎጂ መቀነስ መቻላቸውን ገልጸዋል።

አሁን ላይ እየተከሰተ ያለው ተደጋጋሚ የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ማብቃቱ አይቀርም፤ ነገር ግን መች እንደሚያበቃ ማወቅ አይቻልም ነው ያሉት።

በሰፊና ሁሴን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review