AMN – የካቲት 5/2017 ዓ.ም
በአፍሪካ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እና የጋራ ፍላጎቶችን ለማሳካት አህጉራዊ ተቋማትን እንደ ውጤታማ መሳሪያ መጠቀም እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ “የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በስብሰባው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የአፍሪካ የወደፊት እጣ ፋንታ በጋራ ፈቃደኝነት እና ተግባር ላይ የተመሰረተ ነው።
ለዓለም ፈተና የሆኑትን ጽንፈኝነት እና ጂኦፖለቲካዊ ፉክክር እየታየ መሆኑን ገልጸው፥አፍሪካም በዚሁ በርካታ ግጭት ማስተናገዷን ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ሀገራት በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መድረኮች ትብብርን እና አጋርነትን ማስቀደም እንዳለባቸው አመላክተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ተቋማት ሪፎርም መደረግ እንዳለባቸው እና በዚህም የአፍሪካን ጥቅም ያስጠበቁ እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በመሆኑም በአፍሪካ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እና የጋራ ፍላጎቶችን ለማሳካት አህጉራዊ ተቋማትን እንደ ውጤታማ መሳሪያ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ህብረት የ2063 አጀንዳ የአህጉሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ ተስፋን የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንንም በመገንዘብ ከህግ ማእቀፍ በላይ ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና በአባል አገራትም መካከል ጠንካራ አጋርነት መፍጠር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መጭውን ጊዜ በስኬት ለመወጣት ትብብር ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ የአፍሪካ ሕብረት 2063 አጀንዳን ለማሳካት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን በእጥፍ ማሳደግ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ያቀረበችው ጥያቄ ለአህጉሪቱ የኢኮኖሚ አስተዳደር ለመቅረጽ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጧቸው ጉዳዮች በዓለም አቀፍ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ምላሽ እንዲያገኙ የሚያስችል እንደሆነ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።