
AMN – ኅዳር 05/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ በስኳር ሕመም ከሚጠቁት ሰዎች መካከል 67 በመቶዎቹ ሕመሙ እንዳለባቸው እንደማያውቁ በዓለም አቀፉ የስኳር ፌደሬሽን የተደረገው ጥናት ያሳያል።
በየዓመቱ እ.አ.አ ኅዳር 14 ላይ የሚውለው ዓለም አቀፍ የስኳር ቀን በዛሬው ዕለትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ ተከብሮ ውሏል።
“ዓለም አቀፍ የስኳር ቀን” የሚከበረው ኢንሱሊንን ያገኙትን ፍሬድሪክ ባንቲን እና የጓደኛቸውን ቻርልስ ቤስት የትውልድ ቀን የሆነውን ኅዳር 14 ቀን 1922 መሠረት በማድረግ ነው።
ቀኑ መከበሩ የስኳር በሽታን በተመለከተ ሰፊ ግንዛቤ ለመፍጠር ዕድል የሚፈጥር ሲሆን በሽታን መከላከል፣ መመርመር እና መቆጣጠር በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ ያተኮረ ይሆናል።
ዕለቱ ከአንድ ቢሊየን በላይ ለሚሆኑ ሰዎችም በበሽታው ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር ይረዳል።
በፈረንጆቹ 1991 በዓለም አቀፍ የስኳር ፌዴሬሽን እና በዓለም ጤና ድርጅት የተመሠረተው የዓለም ስኳር ቀን በ2006 ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በይፋ “የስኳር ቀን” በሚል እውቅና አግኝቷል።
የዘንድሮው የዓለም ስኳር ቀን “መሰናክሎችን ማሸነፍ፣ ክፍተቶችን መሙላት” በሚል መሪ ቃል ነው የተከበረው።
በአሁኑ ሰዓት በመላው ዓለም 653 ሚሊዮን ሰዎች ከስኳር በሽታ ጋር ይኖራሉ።
በስኳር ከተያዙ 4 ሰዎች መካከል ደግሞ ሦስቱ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ ነው የሚገኙት።
በሽታውን ለመግታት ባለድርሻዎች እና ሌሎችም ኃላፊነት የሚወስዱበት፣ ሁሉም የተመረመሩ ሰዎች ፍትሐዊ፣ አቅምን ያገናዘበ እና ጥራት ያለው ሕክምና እንዲያገኙ ቃል በመግባትም ጭምር ነው ዕለቱ የተከበረው።
የዓለም ጤና ድርጅት አባል ሀገራት የስኳር ሕመምን ለመቀነስ አምስት ግቦችን አስቀምጠው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
እነሱም በ2030 በስኳር ከተያዙ ሰዎች መካከል 80 በመቶዎቹ ተገቢውን ምርመራ እንዲያገኙ፣ የስኳር ምርመራ ካደረጉ 80 በመቶቹ በደማቸው ያለውን የስኳር መጠን መቆጣጠር መቻል፣ 80 በመቶዎቹ የደም ግፊት መቆጣጣር መቻል፣ 60 በመቶ የሚሆኑ በስኳር ሕመም የተያዙ እና ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት ያለፈ ሰዎች ለሞት ተጋላጭነታቸውን የሚቀንስ “ስታቲን” ተሰኘ ሕክምና እንዲያገኙ ማስቻል እንዲሁም የስኳር በሽታ ዓይነት 1 ታማሚዎች 100 በመቶ ኢንሱሊን እንዲያገኙ እና የደማቸውን የስኳር መጠን በራሳቸው መከታተል እንዲችሉ ማስቻል የሚሉ ናቸው።
በዓለም አቀፉ የስኳር ፌድሬሽን የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የስኳር ሕመም አለባቸው። ከአጠቃላይ ሕዝብ መካከልም 3 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆነው ለበሽታው ተጋላጭ ነው።
በዓለም ዙሪያም 50 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ሕመሙ እንዳለባቸው የማያውቁ ሲሆን በተመሳሳይ በኢትዮጵያም በሕመሙ ከሚጠቁት ሰዎች መካከል 67 በመቶዎቹ ሕመሙ እንዳለባቸው እንኳን እንደማያውቁ ጥናቱ አመላክቷል።
በአፍሪካ ደግሞ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑ ሕመሙ ያለባቸው ሰዎች በሕመሙ እንደተጠቁ አያውቁም።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በስኳር ሕመም ከተጠቁ 653 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 80 በመቶዎቹ በታዳጊ ሀገራት የሚኖሩ ናቸው።
የኢትዮጵያ ስኳር ሕሙማን ማኅበር ከተቋቋመ ከ40 ዓመታት በላይ ሆኖታል። በመላው ኢትዮጵያ ባሉ 89 ቅርንጫፎቹም 20 ሺህ ለሚሆኑ ለዓይነት 1 የስኳር ሕመም ተጠቂዎች የመድኃኒት፣ የኢንሱሊን እና የመመርመሪያ መሣሪያዎችን ድጋፍ እንደሚያደርግ ከማኅበሩ የተገኘ መረጃ ያሳያል።
በቂ ያልሆነ የኢንሱሊን ሕክምና፣ ኢንፌክሽን ወይም ሕመም፣ ውጥረት እና ጉዳት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ሌሎችም የስኳር በሽታ መንስኤዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
ያልታሰበ ክብደት መቀነስ፣ የማይጠፋ ድካም፣ የደበዘዘ የዓይን ዕይታ፣ ከመጠን በላይ የመጠማት ስሜት እና ወዘተ ያሉት ደግሞ የበሽታው ምልክቶች እንደሆኑ ሳይንስ ማረጋገጡን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ስኳር በሽታን መከላከል የሚቻል ሲሆነ ክብደት መቀነስ፣ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ዝቅተኛ ካሎሪ አመጋገብ መከተል፣ ማጨስን ማቆም እና የአልኮል መጠጥን መቀነስ አጋዥ ናቸው።
በማሬ ቃጦ
All reactions:
38Sisay Nibretu Wubetie and 37 others