በኢትዮጵያ ንግድን የሚያሳድግ እና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ ስርዓት እየተገነባ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ

AMN – ግንቦት 18/2017 ዓ.ም

51ኛውን የአፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት ዓመታዊ ኮንፈረንስ እና ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ሁነቱን አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተመራጭ የኢንሹራንስ መዳረሻ ለመሆን እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ግዙፍ ጉባኤ ከ93 የአፍሪካና የሌሎች የዓለም ክፍላተ ሀገራት የመጡ የኢንሸራንስ ተቆጣጣሪዎች፣ የመድን አገልግሎት አቅራቢዎች፣ ፖሊሲ አውጭዎች እና የዘርፍ ባለድርሻ አካላት ለአፍሪካ ኢንሹራንስ መጠናከር ስልት የሚቀይሱበት ነውም ብለዋል።

በአፍሪካ ያለው የኢንሹራንስ አሰራር መሻሻል አለበት፥ ዘርፉን የአህጉሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶ ማድረግ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ለፈጠራ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ፣ንግድን የሚያሳድግ እና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ ስርዓት እየተገነባ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም ጠንካራ የፋይናንስ ዘርፍ ቁልፍ መሆኑን እንገነዘባለን ብለዋል።

የኢንሹራንስ ዘርፉ ደግሞ የፋይናንስ ዘርፉ ማዕከል በመሆኑ ወሳኝ እርምጃዎችን እየወሰድን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም ፈጠራን ለማሳደግ፣ ውጤታማ ቁጥጥርን ለማጠናከርና የፖሊሲ ባለቤቶችን ለመከላከል ገለልተኛ የኢንሹራንስ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መቋቋሙን አስታውሰዋል።

በቅርቡ መንግስት የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን አጠቃቀም እና ባለቤትነትን በተመለከተ አዲስ ህግ ማዘጋጀቱ በቤት ልማት በመሰረተ ልማት እና በሪል ስቴት ዘርፍ የፋይናንስ እና የኢንሹራንስ አቅሞችን የሚያሳድግ መሆኑን አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተስፋ የሚጣልባት የኢንሹራንስ ገበያ ለመሆን እየሰራች መሆኑን በመግለጽ ኢንቨስተሮች ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ጊዜው አሁን ነው ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review