AMN – ጥር 9/2017 ዓ.ም
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ፈተናዎችን መቋቋም የሚችል ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባቱን የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ተናገሩ።
ባለሙያው ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ዓመታት ከነበረበት በ10 እጥፍ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
ለዕድገቱ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አስታውሰዋል።
በዚህም ፈተናን መቋቋም የሚችል የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት ተችሏል ብለዋል።
በተለይም ባለፉት 4 ዓመታት በዓለም የተከሰተው የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ የዓለምን ኢኮኖሚ መጉዳቱን በማስታወስ ከችግሩ ለመውጣት ሀገራት በርካታ ገንዘብ ማተምን ጨምሮ የተለያዩ የኢኮኖሚ እርምጃዎችን መውሰዳቸውን አውስተዋል።
ነገር ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚ ካደጉ ሀገራት ባነሰ ሁኔታ መጎዳቱን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ሳቢያ ማዳበሪያ እና ነዳጅ እንዲሁም የሌሎች የበርካታ ምርቶች ዋጋ በእጥፍ የመጨመሩን ተፅዕኖ ኢትዮጵያ መቋቋም መቻሏን አብራርተዋል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ባወጣው ሪፖርት፣ ከፈረንጆቹ 2020 ወዲህ ባሉት 4 ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአፍሪካ ካሉ አምስት ትልልቅ ኢኮኖሚዎች ግንባር ቀደም መሆኑን ይፋ ማድረጉን ባለሙያው አስታውሰዋል።
የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ለግሉ ዘርፍ ትኩረት መስጠቱ ለኢኮኖሚው ማደግ አስተዋፅኦ ማበርከቱን በማንሳት ይህም በተግባር መታየቱን ተናግረዋል።
ለአብነትም ከ3 ዓመታት በፊት የባንክ ብድር 90 በመቶ ለመንግሥት ይሰጥ እንደነበር በማስታወስ አሁን ላይ በተቃራኒው ከ70 እስከ 75 በመቶ የባንኮች ብድር ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በተሠሩ ሥራዎች ከነበረበት 36 በመቶ ወደ 16 በመቶ ዝቅ ማድረግ ቢቻልም አሁንም ትልቅ ሥራ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።
ኅብረተሰቡ የዋጋ ግሽበቱን እንዲቋቋም መንግሥት እያደረገ ያለው የድጎማ ሥርዓት ይበል የሚያሰኝ መሆኑን እና የሀገር ውስጥ ምርታማነትን ለመጨመር የተጀመሩ እንደ “ኢትዮጵያ ታምርት” ያሉ እንቅስቃሴዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ አቶ ዘመዴነህ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የዋጋ ግሽበትን ከሚያመጡ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሀገሪቱ የግብይት ሥርዓት ዘመናዊ አለመሆኑ ነው ያሉት ባለሙያው ዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አኳያ በኢትዮጵያ ትልቅ ለውጥ መታየቱን ባለሙያው አውስተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድ እና ልማት ጉባኤ (አንክታድ) ይፋ ባደረገው ሪፖርት ባለፉት አምስት ዓመታት ለተከታታይ 5 ዓመታት ኢትዮጵያ ከአምስቱ ትልልቅ የውጭ ኢንቨስትመንት ከሳቡ ሀገራት አንዷ መሆኗን ማስታወቁን አስታውሰዋል።
ሥራ ፈጠራን በተመለከተ የተናገሩት ባለሙያው፣ መንግሥት ሥራ ፈጣሪ አይደለም ነገር ግን የግሉ ዘርፍ ሥራ እንዲፈጥር ምቹ ሁኔታዎችን ሊፈጥር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።