በእጃቸው ያለውን ወርቅ እንደመዳብ ያልቆጠሩ ሀገራት

You are currently viewing በእጃቸው ያለውን ወርቅ እንደመዳብ ያልቆጠሩ ሀገራት

የሀገር በቀል እውቀቶች ለዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች መስፋፋት፣ ለህክምና እና ለኪነ ጥበብ  ኢንዱስትሪ ዕድገት ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ

ናይሮቢ በሚገኘው ጆሞ ኬኒያታ ዩኒቨርሲቲ ግብርናና ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል ተመራማሪው ዋንጉ ጊቱያ ‘The Role of Indigenous Knowledge in Socio Economic Development’ በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፍ እንዳሰፈሩት ሀገር በቀል እውቀት ማለት በአንድ በተወሰነ አካባቢ በሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ባህል ላይ የተመሰረተ እውቀት ነው፡፡ አንዳንድ ሀገራት ሀገር በቀል እውቀቶቻቸውን በመጠቀም የግብርና፣ የጤና፣ የተፈጥሮ ሃብት፣ የትምህርትና አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ጭምር ለመወሰን ይጠቀማሉም ይላሉ ተመራማሪው፡፡

እነዚህ ሀገር በቀል እውቀቶች በብዙ ዘመናት ልምድ የዳበረና በባህል ውስጥ ሰርጾ ከትውልድ ትውልድ በታሪክ፣ በዘፈን፣ በአባባል፣ በእምነት እና በሌሎች መንገዶች የሚተላለፉ ስለመሆናቸውም ተመራማሪው ያስረዳሉ፡፡ የህንፃ ኪነ ጥበብ፣ የጊዜ ቀመር፣ ፍልስፍና፣ የተራራ ላይ እርከን ስራ፣ መሬትን እያፈራረቁ ማረስና ከቀርከሃና የተለያዩ የቤት ቁሳቁስ መስራት፣ የብረት ቅጥቀጣና ሽመና ስራዎች፣ የመድሐኒት ቅመማ፣ ባህላዊ የእርቅ ስርዓቶች በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የሀገር በቀል እውቀቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አንዳንድ ሀገራትም ለሀገር በቀል እውቀት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የእውቀት ዘርፉ ለሀገር ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ተረድተው በመስራታቸው ከፍሬው እየበሉ ይገኛሉ። እንደ ህንድ ያሉ ሀገራትን ደግሞ በአስረጂነት ጠቅሰን ዘርዘር አድርገን ከተመለከትናቸው የሀገር በቀል እውቀቶች ከልብ ከሰራንባቸው ምን አይነት ትሩፋት እንዳላቸው እንመለከታለን፡፡

በዓለማችን በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ በሆነችው ህንድ የነፍስ ወከፍ የሀገር ውስጥ ምርት እ.ኤ.አ ከ2014 እስከ 2023 ባሉት ጊዜያት በ55 በመቶ አድጓል። ለዚህም የሀገር በቀል እውቀቶች ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አንስቶ እስከ ባህላዊ ህክምናና የፊልም ኢንዱስትሪው ድረስ ያላቸው አበርክቶ አስገራሚ ነው፡፡

ህንድ በተለይም የሀገር በቀል እውቀቶችን ተጠቅማ በዓለም የቅመማ ቅመም ግብይት ላይ እያበረከተች ያለውን ድርሻ እንኳን ለይትን ብንመለከት ጉዳዩን ግልጽ ያደርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 በዓለም የቅመማ ቅመም ግብይት 12 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ ይህ በየዓመቱ በአማካይ 4 ነጥብ 8 በመቶ እድገት እያስመዘገበ ኤዶ እ.ኤ.አ በ2019 16 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ የምግብና ግብርና ድርጅት (ፋኦ) እ.ኤ.አ በ2014 ያወጣው መረጃ መሰረት የ2011 ምርት ዘመን ብቻ የዓለም የቅመማ ቅመም ምርት በገበያ አቅርቦት ረገድ ከዘጠኝ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ እንደሆነ ያሳያል፡፡

የእስያ ሀገሮች በምርትና ፍጆታ ቀዳሚ ሲሆኑ፣ ህንድ ካላት የዓመታት የቅመማ ቅመም ማምረት ታሪክ ጋር ተያይዞ ከ6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የሆነውን ድርሻ ትይዛለች፤ ከዚህ ውስጥም ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው ምርት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ይውላል፡፡ ቻይና በበኩሏ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን በማምረት ሁለተኛ ስትሆን ኢንዶኔዥያ 700 ሺህ ቶን በማምረት ሶስተኛ ሀገር ናት፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ በቅመማ ቅመም ንግድ ላይ የሚሳተፉ ሀገራት ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡ ይህንን የተረዳችው ህንድ ሀገር በቀል እውቀቷን ተጠቅማ በዘርፉ የዓለም ገበያውን እስከመምራት የደረሰ ተሳትፎ እያደረገች ትገኛለች፡፡ የቅመማ ቅመም ቴክኖሎጂዎች በዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃዎች ድርጅት (ISO) ከተመዘገቡት 109 የቅመማ ቅመም፣ ዕፀ-ጣዕምና መዓዛማ ሰብሎች ዝርዝር ውስጥ እስከ 75 የሚሆኑት የሚመረቱት በህንድ ነው፡፡ ለዚህም ህንድ ያሏትን ሀገር በቀልና ባህላዊ ቅመማ ቅመሞች ተጠቅማ እንዴት ውጤታማ ልትሆን ቻለች? ለሚለው ጥያቄ ደግሞ የህንድ የስታንዳርድ ቢሮ (Beurau of India Standards-BIS) ያወጣቸውን መረጃዎች እንመልከት፡፡

የተቋሙ መረጃ እንደሚያሳየው ህንድ ያሏትን የቅመማ ቅመም አዘገጃጀት ሀገር በቀል እውቀትን ችላ ሳትል የግሉ ዘርፍ በቅመማ ቅመም፣ ዕፀ-ጣዕምና መዓዛማ ሰብሎች ዝግጅት ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲያደርግ አሰራር ዘርግተዋል። በሌላም በኩል ባህላዊ እውቀቶችን ዘመናዊ መልክ እንዲኖራቸው ለማስቻል በድህረ ምረቃ ትምህርት እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ለሚሰለጥኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎችና ሳይንቲስቶች ዕድል ፈጥራለች፡፡ ፍላጎቱ ያላቸው ተማሪዎች በዘርፉ ጥናታቸውን እንዲያደርጉ ምቹ መደላድል መፍጠርም ችለዋል፡፡

እንደዚሁም ለቅመማ ቅመም፣ ዕፀ-ጣዕምና መዓዛማ ሰብሎች ዙርያ በሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት ያሉትን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የማላመድና የማባዛት ስራዎች በመሰራታቸውና በዘርፉ የሚሰማሩ ሰዎች  በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ግብርና  (ሆርቲካልቸር) የትምህርት ዘርፍ የሰለጠኑ ባለሙያዎች መሆናቸው በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡

በህንድ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ግብርና (ሆርቲካልቸር) ትምህርት ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት የሰለጠነ የሰው ኃይል የሚያበቃ አንድ ዩኒቨርሲቲ ብቻ የነበረ ሲሆን፣ ከ2005 ጀምሮ በ14 የክልል የግብርና ዩኒቨርሲቲ (State Agricultural University/SAU) እና በሌሎች 32 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በድህረ ምረቃ ደረጃ ትምህርት ይሰጣል፡፡

በቻይናም ሀገር በቀል እውቀት ምን ያህል የኢኮኖሚ ምሶሶ ስለመሆኑ እንለመከታለን፡፡ እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ ቻይና በጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ሲለካ በዓለም ሁለተኛዋ ትልቁ ኢኮኖሚ ባለቤት ናት፤ ይህ ሀብቷ እ.ኤ.አ በ2020 በድምሩ 15 ነጥብ 66 ትሪሊዮን ዶላር (101 ነጥብ 6 ትሪሊዮን የቻይና ዩዋን) ሆነ፡፡ የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው ከ2014 ጀምሮ ቻይና በዓለም ፈጣን እድገት ላይ የምትገኝ ዋና የኢኮኖሚ ባለቤት ሆናለች።

የሀገር በቀል እውቀት በቻይና ልማት ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፤ በተለይም እንደ ዘላቂ የሀብት አስተዳደር፣ የአደጋ ስጋት ቅነሳ፣ የገጠር ማህበራዊ ስራ፣ በአካባቢው ስነ-ምህዳርና መሰል ስራዎች ላይ ሀገር በቀል እውቀቶች ድርሻቸው ወሳኝ ነው፡፡ እውቀቶቹን በመንከባከብ፣ በተገቢው መንገድ በማጥናት፣ ለሀገር ልማትና ለማኅበረሰቡም ግንባታ በመጠቀም በኩል ቻይና ሌላኛዋ ተጠቃሽ ሀገር ናት፡፡ በተለይም ስለዕፀዋት ጥበቃና እንክብካቤ፣ በጥንታዊ ሥዕሎች አሣሣል፣ በቀለማት አቀማመጥና የድንጋይ ጥበብ በማስተማር የሀገሪቱን ጉዞ የሰመረ በማድረግ ረገድ ሀገር በቀል እውቀቶችን በአግባቡ ተጠቅማለች፡፡

እንደ ዓለም ባንክ መረጃ ከሆነ ቻይናውያኑ የሰሩት ወሳኙ ነገር በሀገር በቀለ እውቀቶች ላይ የሚመራመሩትን መደገፍ፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተገቢውን ትኩረትና ክብደት በመስጠት ተግባር ተኮር ሥራዎች ተከታታይነት ባለው መልኩ በስፋት እንዲካሄድ በማድረግ ለሀገር በቀል እውቀቶች ህልውና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡

ኢኮኖሚያቸውን ወሳኝ መሰረት ላይ የጣሉና ‘የራስን ጥሎ የሰው አንጠልጥሎ’ን አሻፈረኝ ያሉ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው ውጤታማ መሆናቸውን ነው፡፡ ጥቂቶቹን ለአብነት ጠቅሰን ጹሑፋችንን እንቋጭ፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት ከአምስት ዓመት በፊት ባወጣው ሪፖርት አውስትራሊያ ከባህላዊ መድሐኒት ብቻ በዓመት 1 ቢሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር፣ ቻይና 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር፣ ጃፓን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር፣ ደቡብ ኮሪያ 543 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር፣ ማሌዢያ 2 ቢሊዮን የማልዢያ ገንዘብ፣ ፊሊፒን 10 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ሲንጋፖር 13 ሚሊዮን የሲንጋፖር ገንዘብ እንደሚያገኙ አስታውቋል፡፡

በአህጉረ አፍሪካም ያለውን ሁኔታ ስንመለከት የደቡብ አፍሪካው ሳን ጎሳ ‘ሁዲያ’ የተባለውን ተክል የባለቤትነት መብት ለእንግሊዝ ኩባንያ በሀያ ሚሊዮን ዶላር የሸጠ ሲሆን ሀገሪቷ ከዚህ ባህላዊ መድሐኒት ሽያጭ በዓመት ሀያ ዘጠኝ ቢሊዮን ራንድ ታገኛለች፡፡ በሌላ በኩል ‘ዴቭልስ ክላው’ ከተባለው ተክል የሚገኘውና ህመምን ለመቀነስ የሚያስችለው ባህላዊ መድሐኒት ለናሚቢያ በዓመት ሁለት ሚሊዮን ዶላር ያስገኝላታል፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review