በኦሮሚያ ክልል ለ4 ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቀቀ

AMN – ታኀሣሥ 10/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ እያካሄደ ይገኛል።

ከ7 ሺ በላይ የማህበረሰብ ተወካዮችም ላለፋት 4 ቀናት ሀገራዊ መግባባት ሊደረስባቸው ይገባል ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ሲመክሩ ሰንብተው ዛሬ አጠናቀዋል።

ተሳታፊዎች ያለምንም ጣልቃ ገብነት በነፃነት እና በመደማመጥ ለሀገር ሰላምና አንድነት መሰረት የሆኑ አጀንዳዎችን ማንሳታቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኦሮሚያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ አስተባባሪ ኮሚሽነር አምባዬ ኡጋቶ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

የአራት ቀናት ቆይታው “እጅግ ተስፋ ሰጪ” የሚባል ስለመሆኑም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

የማህበረሰብ ተወካዮች ለቀጣዩ የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር የሚመካከሩ 320 ተወካዮችን መርጠዋል፡፡

ላለፉት 4 ቀናት ያሰባሰቧቸውን አጀንዳዎችም ለመረጧቸው 320 ወኪሎች አስረክበዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ የሚስተዋለው ነፃነትና በተወካዮች ምርጫ ላይ የሚታየው ግልፅነት አዲስ የዴሞክራሲ ልምምድ ስለመሆኑ ደግሞ የማህበረሰብ ተወካዮች ተናግረዋል።

ተወካዮች በቀጣዮቹ ቀናት የክልል ባለድርሻ አካላት ከሚባሉት ማለትም ከኦሮሚያ ክልል መንግስት አካላት፣ ከማህበራት እና ተቋማት፣ ከታዋቂ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ከሐይማኖት ተቋማት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከአባገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎች ጋር በመምከር የኦሮሚያ ክልል አጀንዳዎችን በመለየት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚያቀርቡ ይሆናል።

በካሳሁን አንዱዓለም

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review