በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ተጠናቀቀ

AMN-ታህሣሥ 15/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ከታህሳስ 7 ጀምሮ ለተከታታይ 9 ቀናት ሲያካሄድ የቆየውን የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ አጠናቋል።

ወደ 8 ሺ የሚጠጉ የክልሉ ተወካዮች ሀገራዊ መግባባት ሊደረስባቸው ይገባል ባሏቸው ጉዳዮች ላይ በተለያየ ምዕራፍ ለዘጠኝ ቀናት መክረዋል።

የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በመጪው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይ ሊመከርባቸው ይገባል ያሏቸውን የጋራ አጀንዳዎች ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክበዋል።

ተሳታፊዎች ያለምንም ገደብ በነፃነት ለሀገር ሰላምና አንድነት መሰረት የሆኑ አጀንዳዎችን ስለማንሳታቸው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል።

የአጀንዳ ማሰባሰብ መርሃግብሩ በርካታ ሰዎች በአንድ መድረክ ተገኝተው የመከሩበት ግዙፍና ስኬታማ መድረክ ነበር ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የኦነግ ሸኔ አባላት በምክክሩ መሳተፋቸውም ታላቅ ስኬት መሆኑን አብራርተዋል።

በመጪው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይ ክልሉን የሚወክሉ 25 ተሳታፊዎችም ተመርጠዋል።

በካሳሁን አንዱዓለም

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review