በኦሮሚያ ክልል እስካሁን ድረስ 4.7 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቀርቧል – አቶ አዲሱ አረጋ

You are currently viewing በኦሮሚያ ክልል እስካሁን ድረስ 4.7 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቀርቧል – አቶ አዲሱ አረጋ

AMN – መጋቢት 26/2017

በኦሮሚያ ክልል እስካሁን ድረስ 4.7 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መቅረቡን በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ገለጹ፡፡

አቶ አዲሱ አረጋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ እንዳሰፈሩት ለ2017/18 የምርት ዘመን 10.5 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን እስካሁን ድረስ 4.7 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቀርቧል:: የተቀረዉ ማዳበሪያም በሚቀጥሉት ወራት ዉስጥ እንደሚቀርብ አብራርተዋል፡፡

የዘንድሮዉ አመት የማዳበሪያ አቅርቦት ከባለፈዉ አመት የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር የ2 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዳለዉና የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት እንደማይኖር ጠቁመዋል፡፡

ከማዳበሪያ ዋጋ ጋር በተያያዘም ከዉጭ ምንዛሬ፤ ከሎጂስቲክስና ከአለም አቀፍ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ አንጻር ጭማሪ መኖሩን አንስተዋል፡፡

ከዚህ የተነሳም የፌደራል መንግስት ለግብርናዉ ዘርፍ በሰጠዉ ትኩረት በአንድ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ላይ የ 3ሺህ 700 ብር ድጎማ ማድረጉን አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡

በዚህ አመት ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ በ5ሺህ 845 ብር እንዲሁም ዳፕ በ 7ሺህ 778 ብር እየረበ ነዉ፡፡

መንግስት በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ድጋፍ ባያደርግ ኖሮ ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ከ 9ሺህ 545 ብር እንዲሁም ዳፕ የአፈር ማዳበሪያ በ10 ሺህ 478 ብር ይሸጥ እንደነበረም ገልጸዋል፡፡ የፌደራል መንግስት ለክልሉ እየቀረበ ባለዉ የአፈር ማዳበሪያ ላይ ድጋፍ በማድረጉ አርሶ አደሮች የ38 ቢሊዮን ብር ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ በዛሬዉ እለት በምስራቅ ሸዋ ዞን የማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት የስራ እንቅስቃሴን መጎብኘታቸዉን አብራርተዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review