በኦሮሚያ ክልል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተደረጉ ማሻሻያዎች ውጤት እያመጡ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

You are currently viewing በኦሮሚያ ክልል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተደረጉ ማሻሻያዎች ውጤት እያመጡ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

AMN – መጋቢት 29/2017

በኦሮሚያ ክልል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተደረጉ ማሻሻያዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን የክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ከተማ አንድ ሺህ 402 የእርሻ ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች እና ለማህበራት አስረክቧል።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በወቅቱ እንደገለጹት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤታማ የማሻሻያ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

ከዚህ በፊት ለአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማነቆ የነበሩ አሰራሮችን በማሻሻል በግብርና ዘርፍ እድገት እየተመዘገበ መሆኑን አመልክተዋል።

ለአብነት ከዚህ በፊት ትራክተሮችና ሌሎች የግብርና መሳሪያዎች ከውጭ ሲገቡ ከፍተኛ ቀረጥ ይጣልባቸው እንደነበር ጠቅሰው አሁን ላይ የግብርና መሳሪያዎችን ከታክስ ነፃ በሆነ መንገድ በማስገባት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የክልሉ አርሶ አደር የእርሻ መሳሪያዎችን በብድር እንዲያገኝ እድል መመቻቸቱንም ጠቅሰዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ በበኩላቸው በክልሉ በትኩረት እየተተገበሩ ካሉ ተግባራት መካከል የግብርና ሜካናይዜሽን አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በተሰሩ ሥራዎች በምርትና ምርታማነት እድገት ላይ ለውጥ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

እስካሁን ሻሸመኔ በሚገኘው በኬኛ የግብርና መሳሪያዎች ማምረቻ በኩል ብቻ ከ3ሺህ 500 በላይ ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች፣ ለማህበራትና ለሌሎች ማስረከብ እንደተቻለ ጠቅሰው በአሁን ወቅት በክልሉ 8ሺህ ትራክተሮች እንዳሉ ጠቁመዋል።

ትራክተር ከተረከቡ አርሶ አደሮች መካከል በቦረና ዞን የድሬ ወረዳ ነዋሪው ካራ ዳባቲቻ አስር አርሶ አደሮች ሆነው በኩታ ገጠም ከ20 ሄክታር በላይ መሬት እያለሙ መሆኑን ጠቁመው እስካሁን በበሬ እንደሚያርሱ ገልጸዋል።

አሁን ያገኘነው ትራክተር፣ ጉልበትና ጊዜያችንን ቆጥበን በወቅቱ አርሰን በወቅቱ እንድንዘራና ምርታማ እንድንሆን ያስችለናል ብለዋል።

በምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ የሀዊ አባያ ማህበር ሊቀ መንበር ወጣት አየናቸው አለማየሁ በበኩሉ ለአስር ሆነው በ35 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ አዝርዕትና አትክልቶችን እያመረቱ መሆኑን ተናግሯል።

እስካሁን ትራክተር በመከራየት እንደሚያርሱ ገልጾ አሁን ያገኘነው ትራክተር በሥራችን ላይ መነሳሳት የሚፈጥርልን ነው ብሏል፡፡

በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም አርሶ አደሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review