በከተማዋ ምክር ቤት የተዳሰሱ አንኳር ጉዳዮች

You are currently viewing በከተማዋ ምክር ቤት የተዳሰሱ አንኳር ጉዳዮች

   •   ከተማዋ የዜጎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በምሳሌነት የምትጠቀስ ሆናለች

   •   በመዲናዋ “መሶብ” የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቅርብ ይጀመራል

                                      

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ሚያዝያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት በዓድዋ ድል መታሰቢያ በሚገኘው የምክር ቤቱ አዳራሽ በተካሄደው ጉባኤ የምክር ቤት አባላት በመራጭ ተመራጭ መድረክ ከህዝብ የተሰበሰቡ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

በከተማዋ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ እያደረጓት ነው። የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ከተማዋን በማዘመን፣ ገፅታዋን በመቀየር፣ የማህበረሰቡን የስራ ባህል በመቀየር፣ ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ በአድናቆት ተናግረዋል፡፡ ተቋማትን በማስዋብና ለአገልግሎት ምቹ በማድረግ፣ ዋጋ በማረጋጋት፣ በተለያዩ ሰው ተኮር ተግባራት የተከናወኑ ስራዎች የሚበረታቱ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በርካታ የሚያስመሰግኑ ስራዎች ቢከናወኑም፤ አሁንም ክፍተቶች እንደሚታዩ የምክር ቤት አባላት አንስተዋል፡፡ የህብረት ስራ ማህበራት የሚያቀርቧቸው የፋብሪካ ምርቶች ላይ ከፍ ያለ የዋጋ ጭማሪ ይታያል። አሰራራቸው ላይ ኦዲት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በእሁድ ገበያዎችም የሚፈለገውን የምርት ዓይነትና በተለጠፈው ዋጋ በመሸጥ ረገድ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል፡፡ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በጥራትና ፍጥነት ከማከናወን፣ ውሃን ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ከማሰራጨት፣ በዶሮ እርባታ ላይ የመኖ አቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

በተቋማት የሚሰጠው አገልግሎት ነዋሪውን የሚያረካ እንዲሆን የተሰሩ መልካም ስራዎች ቢኖሩም በአገልግሎት ሰጪዎች ዘንድ የአስተሳሰብ ችግር እንደሚታይና ሌሎች ጥያቄዎች ከምክር ቤት አባላት ተነስተው ምላሽና ማብራሪያዎች ተሰጥቶባቸዋል፡፡ እኛም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የሰጡትን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ 

የኮሪደሪ ልማት

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ አዲስ አበባ ለነዋሪዎችና ጎብኚዎች ምቹና ተስማሚ ከተማ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል።  ‘የኮሪደር ልማት ከተማዋን እየለወጠ ነው’፤ ሕዝቡም የኮሪደር ልማቱ ትሩፋት እንዲደርሰው በመሻት፣ ልማቱ መቼ ነው ወደእኛ አካባቢ የሚመጣው ብሎ እየጠየቀን ነው፡፡ ‘አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና አበባ እናደርጋለን’ የሚል ቃል በመግባት፣ በኮሪደር ልማቱም ቃላችንን በተግባር እየፈፀምን እንገኛለን ብለዋል፡፡ 

ከከተሜነት ጽንሰ ሃሳብ አንጻር አንዲት ከተማ፣ በትክክልም የከተሜነት መስፈርት አሟልታለች ተብላ እውቅና የሚሰጣት በአብዛኛው መሰረተ ልማትን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ በተለይም የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት፣ የመንገድ መሰረተ ልማት፣ የመብራት፣ የቴሌኮምና የትራንስፖርት አገልግሎቶች በትልቅ መስፈርትነት ይጠቀሳሉ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ የአረንጓዴ ልማት ሽፋን፣ የከተማ ውበት፣ ንጹህና አረንጓዴ መሆን ከተሜነት የሚለካባቸው መስፈርቶች ናቸው፡፡

አዲስ አበባ ከዚህ የከተሜነት መስፈርት አንጻር ያለችበት ደረጃ ምን ላይ ነች? የሚል ጥናት አስቀድሞ መካሄዱን ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ባስጠናው ጥናት ከዓለም የከተሜነት መስፈርቱ አንጻር በታሰበው ደረጃ አልነበረችም ብለዋል፡፡ የጥናቱ ውጤት እንዳሳየው፣ በመንገድ መሰረተ ልማት አዲስ አበባ ያላት ሽፋን ከሃያ በመቶ በታች ነበር፡፡ የአረንጓዴ ልማት ሽፋን ደግሞ ከ2 ነጥብ 8 በመቶ የበለጠ አልነበረም። ዓለም ላይ ከተሞች በሚለኩበት መስፈርት ግን 30 በመቶ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ከተማ አስተዳደሩም አዲስ አበባን ዓለም አቀፍ የከተሜነት ደረጃ ያሟላች ከተማ ለማድረግ እቅድ ነድፎ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ማህበረሰቡ በጋራ የሚገለገልባቸውና የሚጠቀምባቸው፣ የሚዝናናባቸው ጽዱ ስፍራዎች እጅግ አስፈላጊ ልማቶች ናቸው፡፡ የዓለም አቀፍ የከተሜነት መስፈርትና ስታንዳርዶችም፣ ፓርኮች፣ የአረንጓዴ ሥፍራዎች፣ የልጆች መጫወቻ ቦታዎች፣ ወጣቶች የሚገናኙበት፣ አካልና አዕምራቿውን የሚያበለጽጉበት የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እንዲኖሩ ያስገድዳል፡፡ ከዚህ አንጻር የከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባን ዓለም አቀፋዊ በሆኑ መስፈርቶች ላይ በመመስረት ተወዳዳሪ ለማድረግ፣ እንዲሁም ህዝቡም በዚህ ዝመና ተጠቃሚ እንዲሆንና ህይወቱ እንዲሻሻል የማድረግ ስራዎችን ነው እየሰራን ያለነው ብለዋል፡፡

የመጸዳጃ ቦታዎችና የሕዝብ መገልገያ ቦታዎችን ስናይ ከተማችን ላይ ትልቅ ለውጥ እየመጣ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋን 2 ነጥብ 8 በመቶ የነበረው ወደ 20 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ የተመዘገበው ውጤት የዚህ ዓመቱን የልማት ስራዎችን የማያካትት ሲሆን፣ የዚህ ዓመቱ ሲጨመር  ከ20 በመቶ ያልፋል፤ በአጭር ጊዜም የከተሜነት ስታንዳርድ የሆነውን 30 በመቶውን ለማሳካት ቀንና ሌሊት ተግተን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

የምንሰራው ሥራ በዋናነት የዜጎችን ሁለንተናዊ ህይወት የተሻለና የዘመነ ለማድረግ ነው፡፡ እንዲሁም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከዚህ በፊት ያጋጥማቸው የነበረው እንደ ጎርፍ አደጋና ተያያዥ ችግሮችንም ከስር መሰረታቸው የሚፈቱ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

የከተማዋንም የመንገድ ሽፋን በማሳደግ ረገድ አበረታች ለውጥ መምጣቱን ከንቲባዋ ጠቅሰዋል፡፡ 80 በመቶ የሚሆነው የከተማዋ ነዋሪ በእግሩ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ከዚህ አኳያ መንገዶችን ለተሽከርካሪ ብቻ ሳይሆን ለሰውም እንዲሆኑ ለእግረኛ መንገድ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ በደሀውና ሀብታሙ መካከል ፍትሀዊ የሆነ አጠቃቀም እንዲኖር እየተሰራ ነው፡፡

በኮሪደር ልማት ምዕራፍ አንድና ምዕራፍ ሁለት በ100 ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል። ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች እንደገለፁት፣ ከተማን ማስዋብ የቅንጦት ጉዳይ አይደለም፡፡ ለነዋሪዎች ውብ፣ ንጹህ የመኖሪያ አካባቢ መፍጠርና የመኖሪያ ቤት ማቅረብ የግድ ነው፡፡ ለጤና፣ ሰላማዊ ግንኙነትና ትስስር ጠቃሚ ነው፡፡ የህዝቡ ገቢ አብሮ ያድጋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ መሳካት የነዋሪዎች ተሳትፎና ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እየተጫወተ እንደሚገኝ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አንስተዋል፡፡ በመቶ ሚሊዮኖች ሊወጣ የነበረው ወጪ የስራ ተቋራጮች ማሽነሪዎችን በነፃ በማቅረብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በበጎ ፈቃደኝነት በጉልበትና በእውቀት ድጋፍ ማድረጋቸውን አብራርተዋል፡፡  

የኑሮ ውድነት

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት፣ በከተማዋ የሚታየውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ የምርት አቅርቦት ለማሳደግ በከተማዋ በአራት መግቢያ በሮች ላይ ትላልቅ የገበያ ማዕከላት ተገንብተው የግብርና ምርቶች ከተለያዩ አካባቢዎች እየቀረቡ ይገኛሉ። በግብርና ምርቶች ግብይት ላይ ያለው የደላላ ሰንሰለትን መበጣጠስ ተችሏል። በተያዘው በጀት ዓመት የላፍቶ እና ለሚ ኩራ ቁጥር ሁለት የገበያ ማዕከላት ተጠናቅቀው ወደ ስራ ይገባሉ፡፡

የእሁድ ገበያም ሌላው ዋጋን ለማረጋጋት፣ ነዋሪው ትኩስ የግብርና ምርቶችን በየአካባቢው እንዲያገኝ የተዘረጋ አማራጭ መሆኑን ያነሱት ከንቲባዋ፣ ከ200 በላይ የሚሆኑ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ከጥራትና ዋጋ ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን በመፈተሽ መፍትሔ እየተሰጠ እንደሚሄድ ጠቁመዋል፡፡

ከተማዋ ሸማች ብቻ ሳትሆን አምራች እንድትሆን በጠባብ ቦታ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በከተማ ግብርና እና ሌማት ትሩፋት ነዋሪው እንዲሰማራ በማድረግ ውጤታማ ስራ መከናወኑን ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አንስተዋል፡፡

በዶሮ እርባታ በርካታ ነዋሪዎች ተደራጅተው የቤተሰባቸውን ፍጆታ ከመሸፈን እስከ ገበያ ምርት እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ የመኖ ዋጋ ንረትን ለመፍታትም አሁን ያለው የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በቂ ስላልሆነ በተጨማሪነት ለመገንባት ጥረት ይደረጋል፡፡

የፍጆታ እቃዎች የዋጋ ጭማሪ ጋር በተያያዘም፣ ግብረ ሀይል ተደራጅቶ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚሞክሩት ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር ይደረጋል። ጎን ለጎን ህግና ስርዓትን አክብረው ህብረተሰቡን ሳይጎዱ እንዲሰሩ ውይይት በማድረግ ውጤት እየተገኘ መሆኑንም ከንቲባዋ ጠቁመዋል፡፡

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የከተማ አስተዳደሩ ድጎማ እያደረገ እንደሚገኝ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አንስተዋል። አዲስ አበባ በለውጡ ዘመን ዜጎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመስራት በምሳሌነት የምትጠቀስ ከተማ ሆናለች። አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ በመመገብ፣ ለተለያዩ ማህበራዊ ችግር የተጋለጡና ደጋፊ የሌላቸው 35 ሺህ ዜጎች፤ በ26 የምገባ ማዕከላት በቀን አንድ ጊዜ ምግብ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 316 መስራት የሚችሉት ሴቶችና ወጣቶች ስልጠና ወስደው ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡

የህብረት ስራ ማህበራት ላይ ጠንካራ ሪፎርም መደረጉን ያነሱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ከዋጋ ጭማሪ ጋር በተያያዘ ባስቀመጡት ዋጋ የሚያቀርቡ መሆኑን ኦዲት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የከተማዋ አስተዳደር የትራንስፖርት ዘርፉን ለመደገፍ በዓመት ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ ያደርጋል፡፡ በተለይ ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት የሚወጣው ወጪ ቀላል እንዳልሆነ እና የከተማ አውቶብሶችም በሚሰጡት አገልግሎት የሚጠየቀው ክፍያም አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማቀላጠፍ በመንግስትና የግል አጋርነት በግል ቱር ኦፕሬተር 100 የኤሌክትሪክ አውቶብሶች በማሰማራት አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ እየተሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡

ማህበራዊ

የመኖሪያ ቤት ከማቅረብ አኳያ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ 5 ሺህ 600 ቤቶች ተገንብተው በመልሶ ማልማት ለተነሱ እና የቤት ጥያቄ ሲያነሱ ለነበሩ ዜጎች ተሰጥቷል፡፡ በኮሪደር ልማት ለተነሱት 9 ሺህ 700 ቤቶች ማቅረብ ተችሏል። ምንም ቤት ላልነበራቸውና በደባልነት ይኖሩ ለነበሩ 2 ሺህ ነዋሪዎች በመጠለያ መልክ የተሰሩ ቤቶችን እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል፤ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፡፡

አገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር

ከንቲባዋ እንደገለፁት፣ የአውቶብስ ተራ – መሳለሚያ – 18 ማዞሪያ እና ሌሎች የተጓተቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች የነበረባቸውን ችግሮች መፍታት ተችሏል፡፡ ፕሮጀክቶቹ በወሰን ማስከበር ችግር ግንባታቸው በመዘግየቱ፣ ተቋራጮች የጠየቁት የዋጋ ማካካሻ ላይ መግባባት ተፈጥሯል፡፡ አሁንም ‘ዋጋ አያዋጣንም፤ የዋጋ ማካካሻ ያስፈልጋል’ የሚል ካጋጠመና ከአቅም በላይ ከሆነ በራስ አቅም ለመጨረስ እንደ ሁለተኛ እቅድ በመያዝ መንገዶቹን ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

የአርሶ አደር መብት ፈጠራ ጋር ተያይዞ ይዞታቸውን ያለ አግባብ የተነጠቁ አርሶ አደሮችን ጥያቄዎችን ለመመለስ ተሰርቷል፡፡ አላግባብ ጥቅም ለማግኘት የሚሞክሩ ያጋጠሙ ሲሆን ከታች ጀምሮ በመገምገምና የሚመለከታቸውን በማሳተፍና መረጃ በማጥራት መፍትሔ መሰጠቱን ወ/ሮ አዳነች ጠቅሰዋል፡፡

የከተማ የህዝብ አውቶብስ አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍም የአዲስ አበባ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ሪፎርም አድርጓል። ከአመራር እስከ ሰራተኛው እንደገና ስምሪት በማድረግ፣ አዳዲስ አሰራሮችን በመዘረጋት፣ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ስርዓትን በመንደፍ መሰራቱን አንስተዋል፡፡

በጥቅሉ አገልግሎትን ከማዘመን አኳያም፤ ምስጋና ለኮሪደር ልማት ይግባውና የቴክኖሎጂ ልማት ዝርጋታው የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ስራው ጊዜ የሚጠይቅ ቢሆንም የተጀመሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው ነው ያሉት፡፡

በአዲስ አበባ ሰሞኑን በፌዴራል ደረጃ የተጀመረው “መሶብ” የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በፍጥነት ለማስጀመር እየተሰራ ነው፡፡ እስከ አሁን በከተማዋ 87 ዋና ዋና እና 262 ንዑስ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ተደግፈው እየተሰጡ ነው። በዋናነት በርካታ ተገልጋይ ያላቸው መስሪያ ቤቶች በአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች  አቤቤ አብራርተዋል፡፡

ሙስናን በመከላከልና በብልሹ አሰራር የተሳተፉትን ተጠያቂ በማድረግ ረገድም አበረታች ስራዎች መሰራቱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አንስተዋል፡፡ ሀብት በማስመለስ ረገድ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ያለ አግባብ ወደ ግለሰቦች ኪስ ሊገባ የነበረ የመንግስትን ሀብት በፍርድ ቤት በመከራከር ማስመለስ ተችሏል። በብልሹ አሰራር ውስጥ የተሳተፉ ወደ 90 የሚሆኑ ከወረዳ እስከ ከተማ ያሉ ኃላፊዎች ከሃላፊነት ማንሳትን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስዶባቸዋል። 1 ሺህ 726 የሚሆኑ ተገልጋይ በሚበዛባቸው መስሪያ ቤቶች በብልሹ አሰራር ተዘፍቀው የተገኙ ሰራተኞች ላይም በተመሳሳይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ 

በአዲስ አበባ “መሶብ” የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቅርብ ስራ ይጀምራል ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እየተንከባለሉ የመጡ በመሆናቸው፣ ችግሮቹን ለመቅረፍ አስተሳሰብ ለውጥ ማምጣትና መደጋገፍ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አዳዲስ የተማሩ ወጣቶችን በማሳተፍ በአዲስ መንፈስ ህዝብን ማገልገል እንዲችሉ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡

የውሃ አቅርቦት

በአዲስ አበባ የውሃ  አቅርቦትና ፍላጎት መካከል መመጣጠን ባለመኖሩ ውሃ በፈረቃ እየተዳረሰ ይገኛል፡፡ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በአዲስ አበባ የውሃ አቅርቦት ከነበረበት 60 በመቶ ያህል ማሳደግ ተችሏል፡፡

ከነዋሪው ቁጥር መጨመር፣ ውሃን የሚፈልጉ አገልግሎቶች መብዛትና የአጠቃቀም ችግር ምክንያት የውሃ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ያነሱት ከንቲባዋ፣ ችግሩን ለማቃለል የተለያዩ የውሃ ፕሮጀክቶች ተነድፈው እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል። 85 ሺህ ሜትር ኪዩቢክ ውሃ በቀን የማመንጨት አቅም ያለው ጩቃላ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት በቅርቡ ወደ ስራ ይገባል። በቀን 75 ሺህ ሜትር ኪዩቢክ ውሃ የማመንጨት አቅም የገርቢ ግድብ ግንባታም እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡

የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ በማስጠበቅ እገዛ እያደረጉ ያሉ በጎ ፈቃደኛ የሰላም ሰራዊት አባላት የሚያስፈልገውን ቁሳቁስና ግብአት እንዲሟላ እንደሚደረግም ከንቲባ አዳነች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ገቢ አሰባሰብና ሀብት አጠቃቀም

በ2017 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ 230 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ነው የታቀደው፡፡ ከሚሰበሰበውና ከሚበጀተው በጀት ውስጥ 71 በመቶ የሚሆነው ለካፒታልና ዘላቂ ልማት የተመደበ ነው፡፡ በጀቱ በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል መደረጉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አንስተዋል፡፡ የመንግስት ሀብት ይባክን የነበረባቸው ግዥና ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይም ለውጥ ማምጣት መቻሉን ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በከተማዋ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ ልማቶችን ለማስቀጠል ለ2017 ዓ.ም የሚውል ከ11 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት እና ልዩ ልዩ ሹመቶችን በማፅደቅ ጉባኤውን አጠናቅቋል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተሮች 

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review