በከተማዋ ውበት የኮሌጁ የጥበብ አሻራ

“ከልጅነቴ ጀምሮ ነበር ስዕል የመሳል ፍላጎቱ የነበረኝ፡፡ ይህን እያደረግኩም ነው ያደኩት፡፡ አስረኛ ክፍል እንዳጠናቀቅኩ እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ገብቼ መሰልጠን ጀመርኩ፡፡ በኮሌጁ ስገባ ከስዕል በተጨማሪ የግራፊክስ እና የቅርፃ ቅርፅ ስልጠናዎችን ወስጃለሁ፡፡ በዚህም ወደ ቅርፃ ቅርፅ ዘርፉ አዘነበልኩ፡፡ በዚህ ዘርፍ ኮሌጁ ብዙ ነገር እንዳውቅ አድርጎኛል” ይላል በቅርፃ ቅርፅ ዘርፍ ስልጠናውን እየተከታተለ የሚገኘው የሶስተኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ሳሙኤል ሐይሉ፡፡

ወጣት ሳሙኤል ከስልጠናው ጎን ለጎን የኮሪደር ልማቱ በስዕል ዘርፍ የስራ እድል እንደፈጠረለት ገልፆልናል፡፡ የኮሪደር ልማት በተከናወነባቸው አካባቢዎች ለግንባታ ዝግጁ በሆኑ ቦታዎች፣ የታጠሩ ቆርቆሮዎች እንዲሁም ድልድዮች ላይ እንደ ዛፍ፣ አበባ የመሳሰሉ የስዕል ስራዎች ሰርቷል፡፡ ለአብነት ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ ኮሪደር፣ ከቀበና እስከ መገናኛ፣ ወሎ ሰፈር፣ ቄራ፣ ጎተራ፣ ሳር ቤትና ሌሎችም የኮሪደር ልማቱ በሸፈናቸው አካባቢዎች የስዕል ስራዎች በመስራት አሻራውን አሳርፏል፡፡ 

ፒያሰ አካባቢ የታጠሩ ቆርቆሮዎች ላይ ያረፉ የሥዕል ሥራዎች

“በቀጣይም በሃገራችን በኪነ ቅርፅ ዘርፍ ያልተሰሩ ብዙ ጉዳዮች ስላሉ በስፋት የመስራት ርዕይ አለኝ፡፡ የኮሪደር ልማቱ ጥሩ እድል አምጥቶልናል፡፡ በምሰራው የኪነ ጥበብ ስራ ተጠቃሚ ከመሆን አልፎ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የራስን አሻራ ማሳረፍም ትልቅ እድል ነው። ይህን ያመቻቸልኝን መንግስት እመሰግናለሁ” ብሏል ሰልጣኝ ሳሙኤል፡፡

ሌላዋ በኪነ ቅርፅ ዘርፍ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ የሆነችው ቤተልሄም መዘምር በልጅነቷ ቤት ውስጥ ስዕል ትስል ነበር፡፡ የነበራትን ተሰጥኦ ለማዳበርም ከኪነ ቅርፅ ስልጠናው ባሻገር በስዕል ዘርፍ በኮሌጁ ለመሰልጠን በቅታለች፡፡ በኮሪደር ልማቱም በመሳተፍ የስዕል ተሰጥኦዋን በመጠቀም የስራ እድል ተጠቃሚ የመሆን እድሉን አግኝታለች፡፡ የስዕል ስራዎቿም አበባ፣ ዛፍ፣ የዱር እንስሳት ምስል ሲሆኑ፤ በመገናኛ፣ ሜክሲኮ፣ ቄራ፣ ሲኤምሲና ሌሎች የኮሪደር ልማት የሚከናወንባቸው ቦታዎች ሰርታለች፡፡

“ተሰጥዖዬን በኮሪደር ልማቱ ማሳየቴ ደስ ብሎኛል፡፡ የምሰራው ስራ እንደሃገር እንዳስብ አስችሎኛል፡፡ ስልጠናዬን ሳጠናቅቅ በቅርፃቅርፅና በስዕል ስራው ጠንክሬ ለመስራት እቅድ አለኝ፡፡” ብላለች ሰልጣኝ ቤተልሄም፡፡

በአብዛኛው በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በተጠናቀቀባቸውና በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ለግንባታ ዝግጁ በሆኑ ቦታዎች የታጠሩ ቆርቆሮዎች ላይ እንዲሁም ድልድዮች አካባቢ ለአይን የሚማርኩ የኪነ ጥበብ ማለትም በስዕልና ቅርፃቅርፅ የተዋቡ ስራዎች እንመለከታለን፡፡ እነዚህ ስራዎች በአንጋፋው የቴክኒክና ሙያ ተቋም በሆነው እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ባፈራቸው የስነ ጥበብ ትምህርት ክፍል ሰልጣኞች የተሰሩ መሆናቸውን በኮሌጁ የቅርፃቅርፅ አሰልጣኝ ሳራ መንግስቱ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በሰጡት መረጃ ገልፀዋል፡፡

እንደ አሰልጣኝ ሳራ ገለፃ፤ በኮሌጁ የስነ ጥበብ ትምህርት ዘርፍ ውስጥ በግራፊክስ፣ በስዕል፣ በቅርፃቅርፅ ስልጠና ይሰጣል፡፡ በኮሌጁ የሚሰለጥኑ ሰልጣኞችም በዘርፉ ባላቸው የተለያየ የሙያ ብቃት በግላቸው ስራዎችን በመስራት የስራ እድል ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡ በኮሪደር ልማቱም ከመገናኛ እስከ ሲ ኤም ሲ፣ ሜክሲኮ፣ መገናኛና ሌሎችም የኮሪደር ቦታዎች የኮሌጁ ሰልጣኞች ለአብነት አበባ፣ ዛፍ፣ የእንስሳት ምስል እና በፋውንቴን ውስጥ የአለት ቅርፃቅርፅ የስነ ጥበብ ስራዎች ሰርተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ በዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ በአንድነት ፓርኮች፣ በብሔራዊ ቤተ-መንግስትና ሌሎችም የስዕልና የቅርፃቅርፅ ስራዎቻቸውን ሰርተዋል፡፡

ኮሌጁ ሰልጣኞች ከስልጠና ጎን ለጎን በሙያቸው በተለያዩ ጊዜያት በሚመጡ የስራ እድሎች እንዲሳተፉ ያደርጋል፡፡ ሰልጣኞች በግላቸውም በሚያገኙት የስራ እድል ባላቸው ተሰጥኦ እየተሳተፉና የስራ እድል ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ በኮሪደር ልማቱ በግላቸው በመሳተፍ የሰሩት የስነ ጥበብ ስራ ለከተማዋ ውበትና መልካም ገፅታ መፈጠር አንድ ማሳያ ነው፡፡ በአብዛኛው በተለያዩ አካባቢዎች የምንመለከታቸው ለከተማዋ ውበት የሚጨምሩ፣ ገፅታን የሚያጎሉ የስነ ጥበብ ስራዎችን የሰሩት ኮሌጁ ያፈራቸው ሰልጣኞች መሆናቸውንም አሰልጣኝ ሳራ ገልፀዋል፡፡

በቅርፃቅርፅና የስዕል ስራዎች ላይ ለመሳተፍ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች መሆን አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ቅርሶቹ ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ እውቀቱ ያለው ባለሙያ ቢሰራ መልካም ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከኮሌጁ የሚሰለጥኑ ከፍተኛ ብቃት ያላቸው በመሆኑ በዚህ ዘርፍ መስራት የሚፈልጉ ተቋማት የኮሌጁ ሰልጣኞች የመስራት አቅም ስላላቸው ከኮሌጁ ጋር በቅንጅት ቢሰሩ ውጤማ እንደሚሆኑ ነው አሰልጣኝ ሳራ የጠቆሙት፡፡

እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ብቃት ያላቸው በርካታ ዜጎችን እያፈራ ያለ ተቋም ነው፡፡ “በሃገራችን በቴክኒክና ሙያ የሠለጠኑ፣ ብቃት እና ክህሎት ያላቸው ዜጎች ስላሉን እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ብንጠቀም ለዜጎቹ የስራ እድልም ለመፍጠር ያስችላል” ይላሉ አሰልጣኝ ሳራ፡፡

በመሆኑም የመንግስትም ሆኑ የግል ተቋማት በስነ ጥበብ ዘርፉ የሚሰራ ስራ ካላቸው በሙያው ብቃት ባላቸው የሰለጠኑ ዜጎች እንዲሰራ እና የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ከኮሌጁ ጋር በትስስር ቢሰሩ መልካም ይሆናል ሲሉ የቅርፃቅርፅ አሰልጣኝ ጥሪ አቅርበዋል።

በከተማዋ በሚከናወኑ የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲሁም የኮሪደር ልማቱ ይዞት በመጣው እድል የኮሌጁ ሰልጣኞች በተዋቡ የጥበብ ስራዎች ለከተማዋ ውበትንና መልካም ገፅታን የሚያላብሱ የኪነ ጥበብ ስራዎችን በመስራት አሻራቸውን አኑረዋል። የኮሪደር ልማቱ ሰልጣኞች ገና ወደ ስራ ዓለም ሳይቀላቀሉ ከስልጠናው ጎን ለጎን የስራ እድልንም ፈጥሮላቸዋል፡፡ የስልጠናው ፍሬም በተግባር የተገለጠ በመሆኑ ኮሌጁ እያከናወነ ያለውን ፍሬያማ የስልጠና ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥል እንላለን፡፡

በስገነት አስማማው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review