በካናዳ በተደረገው ምርጫ የሊብራል ፓርቲ ማሸነፉ ተገለፀ

You are currently viewing በካናዳ በተደረገው ምርጫ የሊብራል ፓርቲ ማሸነፉ ተገለፀ

AMN – ሚያዚያ 21/2017 ዓ.ም

በካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኔይ የሚመራው ሊብራል ፓርቲ የአገሪቱን አጠቃላይ ምርጫ ያሸነፈ ሲሆን የዶናልድ ትራምፕ አቋም ለውጤቱ እንዳገዛቸው ተገልጿል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጥር ወር ጀምሮ የጎረቤት አገር የሆነችው ካናዳን 51ኛዋ የአሜሪካ ግዛት እንደምትሆን በተደጋጋሚ ሲናገሩ የነበረ ሲሆን እነዚህ ተደጋጋሚ አስተያየቶች ሊበራል ፓርቲው ሉዓላዊነታቸውን የማጣት ስጋት ያላቸውን ካናዳውያንን በማሰባሰብ እንዲያሸንፍ እንደረዳው ተገልጿል።

ዶናልድ ትራምፕ ይህንን አቋማቸውን ይፋ ከማድረጋቸው በፊት የወግ አጥባቂው ተወዳዳሪ ፒር ፖሊየቭ ያሸንፋሉ ተብሎ ይገመት ነበር። አገሪቱን ላለፉት አስርት ዓመታት የመሩት የሊብራሉ ፓርቲ አባሉ ጀስቲን ትሩዶ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ምንም ለውጥ ባለማሳየታቸው በፓርቲው ደጋፊዎች ዘንድ ቅሬታ ተፈጥሮ እንደነበርም ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኔይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ላይ ብቻ ሳይሆን በሉዓላዊነቷም ላይ አደጋ መደቀናቸውን በመግለጽ የመራጮችን ልብ ማሸነፍ ችለዋል።

አሜሪካ መሬታችንን፣ የተፈጥሮ ኃብታቸንን እና አገራችንን ትፈልጋለች ያሉት ማርክ ካርኔይ “ከአሜሪካ ጋር የነበረን የቆየ የትብብር ወዳጅነት አብቅቷል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ካርኔይ አገራቸው ከአውሮፓ እና ሌሎች አጋር አገራት ጋር ያላትን ወዳጅነት አጠናክራ እንደምትቀጥል የተናገሩ ሲሆን በመጪዎቹ ቀናት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የሁለቱ ሉዓላዊ እና ነጻ አገራት የወደፊት መጻዒ ዕድል ላይ እንወያያለን ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review