በክልሉ ህዝቡን በማሳተፍ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል -አቶ ከፍያለው ተፈራ

You are currently viewing በክልሉ ህዝቡን በማሳተፍ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል -አቶ ከፍያለው ተፈራ

AMN – ሚያዝያ 1/2017

በኦሮሚያ ክልል ህዝቡን በማሳተፍ በየአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አዘጋጅነት ”የሀይማኖት ተቋማት ሚና ለሰላም ግንባታ እና ለእርቅ” በሚል መሪ ሀሳብ የሰላም ኮንፍረንስ በጅማ ተካሄዷል።

በሰላም ኮንፍረንሱ ላይ የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች፣ የተለያዩ የእምነት ተቋማት ተወካዮች፣ የሀይማኖት አባቶች እና ህዝቡ ተገኝተዋል።

በኮንፍረንሱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ከፍያለው እንዳሉት፥ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ህዝቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን አንስተዋል።

በቀጣይም ሰላምን የማረጋገጥ ስራውን ህዝቡ በየአካባቢው በማገዝ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።

ህብረተሰቡ በየአካባቢው ሰላምና ደህንነትን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን በልማት ስራዎች የሚያደርገውን ተሳትፎም ማሳደግ አለበት ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ በበኩላቸው፥ ህዝቡ ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ በተለያየ መልኩ አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

ክልሉ ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን በተለይም የሀይማኖት አባቶች ከህብረተሰቡ ጋር ሆነው የሰላም ግንባታ ተሳትፏቸውን ማጉላት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፥በየአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን የሀይማኖት ተቋማት እያበረከቱ ያሉት አስተዋጽኦ ትልቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም የሀይማኖት ተቋማት በህዝቦች መካከል ሰላም፣አንድነትና ፍቅር እንዲጎለብት ተከታታይነት ያለው ስራ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኦሮሚያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢና የኦሮሚያ መጅሊስ ፕሬዝዳንት ሼህ ጋሊ ሙክታር በበኩላቸው፥ ህዝቡ ለሰላምና ለልማት በህብረት እንዲቆም የሀይማኖት ተቋማት የድርሻቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል።

ልጆቻችንን የሰላም አስፈላጊነት ጥቅምን እየሰበክን በማሳደግ መዋደድንና ወንድማማችነትን ማንገስ ይኖርብናል ሲሉም ገልጸዋል።

ሀይማኖት የሰላም መሰረት፤ የሰላም ምንጭ ነው፤ ሁሉም ሊጠብቀው ይገባል ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ፓስተር ዲንቃ ሁንዴሳ ናቸው።

በኮንፈረንሱ የተሳተፋ ነዋሪዎችና የሀይማኖት አባቶች በበኩላቸው የሰላም ውይይቱ የሚበረታታና ሁሉንም ለሰላም፣ለፍቅርና ለወንድማማችነት የሚያነሳሳ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review