AMN – የካቲት 4/2017 ዓ.ም
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።
የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ በታርጫ ከተማ እያካሄደ ነው።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር) የአስፈፃሚ ተቋማትን የግማሽ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
በሪፖርቱም ክልሉ ያሉትን የልማት ጸጋዎች በመጠቀም ህዝቡን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ የተደረጉ ጥረቶች ውጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የልማት ሥራዎችን በተቀናጀ ዕቅድ በጥራትና በፍጥነት ለማከናወንና ቀጣይነት ያለውን ዕድገት ለማስመዝገብ የአጭር፣የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ግቦች ተነድፈው እየተተገበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብዓት አቅርቦትና የግብርና ኤክስቴሽን አገልግሎትን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሥራዎች መሰራታቸውንም ጠቅሰዋል።
በዚህም ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በዓይነትና በብዛት በማምረት ክልሉ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን እንዲወጣ ለማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።
እንደ ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር) ገለጻ፥ የገቢ አቅምን በማሳደግ፣ በጀትን በቁጠባ በመጠቀምና በመሰረተ ልማት የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጎልበት በተሰሩ ሥራዎች ውጤት እየተመዘገበ ነው።
በማህበራዊ ዘርፍም የጤናና የትምህርት ልማት ተደራሽ በማድረግና የሚሰጠውን አገልግሎት በጥራት ለማቅረብ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን የማስፋፋት ሥራ መከናወናቸውን አንስተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትና የክልሉን ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል በተሰራው ስራም ለልማት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደተቻለም ተናግረዋል።
ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ፣ ምክር ቤቱ የአስፈፃሚ ተቋማትን ተግባር በመገመገም ግብረመልስ ሲሰጥ መቆየቱን ገልፀዋል።
የህዝብ አስተያየቶች ለመሰብሰብ የሚያስችሉ መድረኮችን የማመቻቸትና የኦዲት ግኝት ሥራዎችን በመገምገም አቅጣጫዎች ማስቀመጡንም ተናግረዋል።
የክልሉ ምክር ቤት ለሁለት ተከታታይ ቀናት እያካሄደ ባለው ጉባኤ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ወንድሙ አመልክተዋል።
የአስፈፃሚ ተቋማት የስድስት ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት፣ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች፣ ደንቦችና አጀንዳዎችን ገምግሞ ማፅደቅ የጉባኤው አጀንዳዎች እንደሆኑም ከወጣው መርሀግብር ለማወቅ መቻሉን ኢዜአ ዘግቧል።