
AMN – ኅዳር 7/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በክረምት ወቅት ባደረገችው ሰፊ የግብርና ስራ ርብርብ በመኸር ወቅት በታሪክ ከፍተኛው የእርሻ መሬት በዘር መሸፈኗን እና ከዚህም ከፍተኛ መጠን ያለው የሰብል ምርት ለመሰበሰብ ዝግጅት መጠናቀቁን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ኢትዮጵያ በሁሉንአቀፍ የልማት ዘርፎች ዕድገትና ብልጽግና መረጋጋጥ የሚያስችል የተጠናከረ ርብርብ እያደረገች ስለመሆኗ ጠቁመዋል፡፡
በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ የማንሰራሪያና ሀገራዊ እመርታን ማጽናት የሚያስችል መሰረት በሚጣልበት በዘንድሮ ዓመት በቁልፍ የልማት ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል በዚህም ውጤት እየተገኘ ቀጥሏልም ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
የግብርና ዘርፍን የጠቀሱት ዶ/ር ለገሰ የዘንድሮ ዓመት ኢትዮጵያ በታሪኳ ከፍተኛ መሬቷን በሰብል የሸፈነችበት ዓመት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ይህንን የሰብል ምርት እስከ መጪው ታህሳስ ወር ድረስ ሙሉ በሙሉ ለመሰብሰብ ርብርብ እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ እንደስሟ እንደሚጠበቅ ዓለምአቀፍ ኃላፊነቷ ደረጃዋን ለማላቅ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ያሉት የኮሪደር ልማት በእርግጠም አዲስ አበባን የዘመነ የከተማ ልማትና ገጽታ እንዲኖራት አድርጓልም ነው ያሉት፡፡
እስከአሁን ባለው ሂደትም የኮሪደር ልማት ከ30 በላይ ለሚሆኑ ከተሞች በተሞክሮነት ተወስዶ እየተተገበረ ይገኛልም ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
ኢትዮጵያ ካላት አንጡራ ህብት እምቅ የስበት አቅም አንጻር የቱሪዝም ዘርፍ የዳበረና ምቹ የመሰረተ ልማት ያለው እንዲሆን በማድረግ ረገድ መንግስት አጠናክሮ የቀጠለው የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት ከወዲሁ ሃብት ማመንጨት ሃገራዊ ኢኮኖሚንም መደጎም የሚችል አቅም ማሳደጋቸውን በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመት የእስካሁን ወራት አዲስ አበባ ከተማ በርካታ ዓለምአቀፍና አህጉራዊ መድረኮችን ስለማስተናገዷ ያወሱት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ፣ በተያዘው የህዳር ወር 10 የሚደርሱ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ መድረኮች በአዲስ አበባ እንደሚደረጉም አስታውቀዋል፡፡
በአቡ ቻሌ